በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል- ዶክተር ዓለሙ ስሜ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በሁሉም ዘርፎች ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችን ማጠናከር ይገባል- ዶክተር ዓለሙ ስሜ
ሆሳዕና፤ መጋቢት 14/2016 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሁሉም ዘርፎች ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ እየተከናወኑ ያሉትን ሥራዎች ማጠናከር እንደሚገባ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ ተናገሩ።
በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዶክተር ዓለሙ ስሜ የተመራው የፌዴራል የድጋፍና ሱፐርቪዥን ቡድን በክልሉ ባካሄደው የመስክ ምልከታ ላይ ለክልሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ግብረ መልስ ሰጥቷል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ክልሉ አዲስ የተቋቋመ ቢሆንም የውስጥ ሰላሙን በማስጠበቅና ህዝብን በማስተባበር የተሻለ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን በተግባር መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ክልሉ ለሰላም ግንባታ፣ ለግብርና ልማት፣ ለሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር፣ የውስጥ ገቢን ለማሳደግና ለሌሎች የልማት ሥራዎች የሰጠው ትኩረትና የተመዘገበው ውጤት አበረታች ነው ብለዋል።
ቡድኑ ተንቀሳቅሶ የተመለከታቸው የተጀመሩ የልማት ሥራዎች በተሻለ ሂደት ላይ እንዳሉ ግንዛቤ መያዙን የጠቀሱት ዶክተር ዓለሙ፣ ዘላቂነታቸውን ለማረጋገጥ ጥረቱ መጠናከር ይገባዋል ብለዋል።
በተለይም የክልሉ አመራር አባላት ህዝብን በማስተባበርና በተቀናጀ መንገድ የጀመሩትን አበረታች የልማት ተግባራት ማጠናከር ይኖርባችኋል ነው ያሉት።
"በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የተሰጠው ልዩ ትኩረት መጠናከር አለበት" ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለልዩነት በር የሚከፍቱ ዕሳቤዎች በማክሰም ገዢ ትርክቶችን ማዳበር ይገባል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነርና የቡድኑ አባል አቶ ዳገቶ ኩምቤ በበኩላቸው፣ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በሁሉም የልማት መስኮች ጥሩ ውጤት እየተመዘገበ መምጣቱን መመልከታቸውን ተናግረዋል።
በተለይም በአዲስ ዕሳቤ የተጀመሩ የግብርና ልማት እንቅስቃሴዎች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርና በበጋ መስኖ ልማት የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ዘርፎቹ ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው አበረታች እንደሆነ ገልጸዋል።
አቶ ዳገቶ እንዳሉት፣ በክልሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እንዲሁም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ አፈጻጸም የተሻለ ቢሆንም ለችግኝ ተከላና እንክብካቤ ሥራ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል።
ክልሉ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮች በአግባቡ ለመጠቀም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጀምሮ የመስሪያ ቦታዎችና የተዘጋጁ መሬቶች መኖራቸው ዘርፉን ለማነቃቃት ማስቻሉንም አስረድተዋል።
በጤናና በትምህርት ዘርፎች ለውጥ ለማምጣት በማህበረሰብ ተሳትፎ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆናቸውን ማየታቸውን ገልጸው፣ ተግባራቱ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።
በትምህርት ተሃድሶ ተግባራትና በማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ላይ የታየውን የተሻለ አፈጻጸም ማጠናከር ይገባል ብለዋል አቶ ዳገቶ።
በክልሉ በሁሉም ዘርፎች የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ናቸው።
"ቡድኑ በክልሉ ተገኝቶ ተጨባጭ የሥራ ውጤቶችን ተመልክቶ ግብረ መልስ መስጠቱ ለቀጣይ ስራችን ስንቅ ነው" ብለዋል።
በክልሉ ህብረተሰቡ ሰፊና የቆዩ የልማት ጥያቄዎች ፈታኝ ቢሆኑም፤ ህዝብን በማሳተፍ በተከናወኑ ሥራዎች በአጭር ጊዜ ምላሾች መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
የክልሉ የሰላምና ፀጥታ በማረጋገጥ በኩል አመራሩና ህዝቡ ተቀናጅተው በመስራቱ የተገኘው ውጤት ሌሎች የልማት ስራዎችን በተረጋጋ መልኩ ለማከናወን አቅም መሆኑን አስረድተዋል።
ክልሉ ያሉትን የልማት አማራጮች በመለየት ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የጀመራቸውን ሁለንተናዊ የልማት ሥራዎች አጠናክሮ እንደሚያስቀጥልም ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
በበጀት ዓመቱ በክልሉ 77 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መጽደቃቸውን ያስታወሱት አቶ እንዳሻው፣ የገበታ ለትውልድ መርሃ ግብር ትግበራን በተመለከተ ለጥያ ትክል ድንጋይ በሁለት ባለሀብቶች የተለያየ ፕላን መቅረቡንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተግባር እንደሚገባ ገልጸዋል።
የፌደራል የድጋፍና ሱፐርቪዥን ቡድን በሆሳዕና ከተማ ግብረ መልስ ለመስጠት በተዘጋጀ መድረክ የክልሉ ካቢኔና ሌሎች አባላትም ተገኝተዋል።