የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዘውን እንሰት በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል - ተመራማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያግዘውን እንሰት በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል - ተመራማሪዎች
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 14/2016(ኢዜአ)፦ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም ያለውና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዘውን እንሰት በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ።
ዋና መቀመጫውን እንግሊዝ አገር ያደረገው ሮያል በተሰኘው የእጽዋት ምርምር ተቋም የዘርፉ ተመራማሪዎች፤ እንሰት የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅም እንዳለውና የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽዖ ያደርጋል ብለዋል።
በተቋሙ የእጽዋት ባህሪና ጥቅም ጥናት ቡድን መሪ ጀምስ ቦሬል ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርና ብዝኃ ሕይወትና አዝርት ስብጥር እምቅ አቅም ካላቸው አገሮች አንዷ መሆኗን ተናግረዋል።
የምርምር ተቋሙ ላለፉት 40 ዓመታት እንሰት ድርቅንና የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ያለውን ጥንካሬ በተመለከተ ጥልቅ ምርምር ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው ኢትዮጵያ በዓለም ልዩ የሆነው የእንሰት ምርት መገኛ መሆኗን ገልጸዋል።
እንሰት ወቅት ሳይጠብቅ በማንኛውም ጊዜ መመረት የሚችልና ለረዥም ጊዜ በማስቀመጥ ለምግብነት የመዋል ከፍተኛ አቅም እንዳለውም ጠቁመው በተለይም የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ትልቅ ሚና ይኖረዋል ያሉት።
እንደ ተመራማሪው ገለጻ፤ ሮያል የእጽዋት ምርምር ተቋም ላለፉት ስምንት ዓመታት የእንሰት መገኛን ለመለየት እንዲሁም ድርቅን የመቋቋም አቅሙን ለማወቅ ጥናት ሲያካሂድ ቆይቷል።
ይህንንም ተከትሎ በተለይም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን የተለያየ ዝርያ ያላቸውና የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም አቅም ያላቸው የእንሰት እይነቶችን መለየታቸውን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ 300 የአርሻ ቦታዎችን መጎብኘታቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ብዝኃ ህይወት ጥበቃ ላይ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ መሆኑን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል።
አርሶ አደሮች ለእንሰት ምርት እያደረጉ ያለው ጥበቃና እንክብካቤ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመዋል።
እንሰት በቀጣይ ከፍተኛ የምርት መጠን በመስጠትና ድርቅን ለረዥም ጊዜ በመቋቋም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የሚጣጣም የምርት አይነት እንደሚሆን ጠቅሰዋል።
አርሶ አደሮች የእንሰት ምርት ዝርያን በመጠበቅና እንክብካቤ በማድረግ በርካታ ዝርያዎችን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
እንሰት ድርቅና የተለያዩ በሽታዎችን የመቋቋም ከፍተኛ አቅም ያለው ሲሆን በኢትዮጵያ ከ20 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዋና ምግብ ሆኖ እንደሚያገለግል መረጃዎች ያመላክታሉ።