በትግራይ ክልል አገልግሎት አቁመው የነበሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል አገልግሎት አቁመው የነበሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ ነው-የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል
መቀሌ፤ መጋቢት 14/2016 (ኢዜአ)፡- በትግራይ ክልል አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደተናገሩት በክልሉ የሚገኙ የኃይል ማመንጫዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለይቶ በመፍታት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ለዚህም በተከዜ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እና በአሸጎዳ የንፋስ ሃይል የጥገናና እድሳት ሥራ በማከናወን ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም የኃይል ማመንጫዎቹን አቅም ለማሳደግ የፍተሻና የጥገና ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው አቶ ሞገስ ያስታወቁት።
የአሸጎዳ የንፋስ ኃይል ማመንጫ 84 ተርባይኖችን ሥራ ለማስጀመር በተደረገ ፍተሻና ጥገና እስካሁን ድረስ የ27 ተርባይኖች የጥገና ሥራ ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ የሚያመነጩት 25 ሜጋ ዋት ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት መግባት ጀምሯል ብለዋል።
የቀሩትን የንፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይኖች ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፣ የተርባይኖቹ ፍተሻና ጥገና ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ 120 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት እንደሚያስችሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የተከዜ የኃይል ማመንጫ ጣቢያን ወደ ሥራ ለማስገባት የጥገና ሥራው እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በጣቢያው ሃይል ከሚያመነጩት አራት ተርባይኖች በአሁኑ ወቅት ሁለቱ ብቻ 150 ሜጋ ዋት ኃይል እንደሚያመነጩ የገለጹት አቶ ሞገስ፣ ቀሪዎቹን ተርባይኖች ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በብልሽት ምከንያት ሥራ ያቆሙትን ተርባይኖች ሥራ ለማስጀመር የገጠመውን የመለዋወጫ ዕቃዎች ችግር ለመፍታት በሂደት ላይ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ለተርባይኖቹ የሚካሄደው ጥገና ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ጣቢያው 300 ሜጋ ዋት ለማመንጨት እንደሚችልም አቶ ሞገስ ተናግረዋል።
በክልሉ የሚገኙት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫዎች ወደሥራ መግባት ወደብሔራዊ የኃይል ቋት የሚገባውን ኃይል እና የአገሪቱን የኤሌክትሪክ አቅርቦት በማሳደግ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን እንደሚያሳልጥም አቶ ሞጎስ አመልክተዋል።