ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ አምራቾች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ወደ ሥራ ሊገባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ አምራቾች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ወደ ሥራ ሊገባ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2016 (ኢዜአ)፦ ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ አምራቾች ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችል ስትራቴጂ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።
የሥራ ፈጣሪ ባለቤቶች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላይ ሊተገበሩና ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚችሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያስተዋውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቱ እድገት እንዲፋጠን የበኩላቸውን እየተወጡ ነው።
ኢዜአ በመዲናዋ ተዘዋውሮ ያነጋገራቸው የፈጠራ ባለቤቶችም፤ ያስተዋወቋቸው ቴክኖሎጂዎች በተሰማሩበት የሙያ መስክ ውጤታማነትን መጨመሩን ይናገራሉ።
ከዚህም ባሻገር የሥራ ዕድሎችን በማመቻቸት ረገድ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ይገልፃሉ።
አቶ ከበደ ላቀው ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ በማድረግ የባለቤትነት መብት እንዳላቸው ይናገራሉ።
የፈጠራ ኃሳቡን መነሻ በማድረግ በሚሰሩት ሥራ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር በዘርፉ በአገር ውስጥ ተኪ ምርት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ወጪን መቀነስ መቻሉን ይገልፃሉ።
ፈሳሽ ማዳበሪያው የአፈር ለምነትን የሚጨምር፣ የምርት ጤንነት እንዲሁም የአካባቢ ደኅንነትን የሚጠብቅ መሆኑን አንስተዋል።
የወተት ተዋፅዖ ማቀነባበሪያ መሣሪያ በመሥራት የፈጠራ ባለቤት የሆነው ወጣት አበራ ግርማ፤ በዘርፉ በሰው ጉልበት የሚከወኑ ተግባራት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲተኩ ማድረጉን ይገልፃል።
የወተት ማቀነባበሪያ መሣሪያው አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እስከ 30 ሊትር የሚሆን ወተት በማቀነባበር የአይብ፣ የቅቤና የአጓት ምርቶችን እንደሚያቀርብ ነው ያስረዳው።
ቴክኖሎጂው ጊዜና የሰው ኃይል በመቆጠብ ምርትና ምርታማነትን እንደሚጨምር ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኤሊያስ መሃመድ፤ ለፈጠራ ባለቤቶች የምዝገባና የጥበቃ አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
ተቋሙ የሚሰጠው እውቅና የፈጠራ ባለቤቶቹ ወደ ሥራ ገብተው ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ እንዲያደርጉና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ተዓማኝነት እንዲኖራቸው ያስችላል ብለዋል።
እንዲያም ሆኖ ለፈጠራ የሥራ ባለቤቶች ያሏቸውን ኃሳቦችና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ተግባር እንዲለውጡ የሚመለከተው አካል ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ይህንንም ተከትሎ አሁን ላይ የተኪ ምርት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግባት የትግበራ እቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰዋል።