በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ሥርቆት የኤሌክትሪክ ኃይልን በአግባቡ ለማዳረስ እንቅፋት እየፈጠረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ሥርቆት የኤሌክትሪክ ኃይልን በአግባቡ ለማዳረስ እንቅፋት እየፈጠረ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2016(ኢዜአ)፦ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ላይ እየተፈጸመ ባለው ዝርፊያ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ግሪዶች ደካማ እንዲሆኑና ሕብረተሰቡ በሚፈልገው መጠን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይደርሰው እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እየተባባሰ በመጣው የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ-ልማት ሥርቆት ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰ ነው።
ሥርቆቱ የሚፈፀመው ደግሞ ተቋሙ የኤሌክትሪክ ኃይልን በተገቢው መንገድ ለማዳረስ ጠንካራ ግሪድ እንዲኖር በሚያደርግበት ወቅት መሆኑን ገልፀዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመሠረተ-ልማቱ ላይ የሚፈፀመው ሥርቆት እየተባባሰ መምጣቱ ሕብረተሰቡ በአግባቡ አገልግሎቱን እንዳያገኝ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2015 ዓ.ም. ብቻ በኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማት ሥርቆት ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ኪሳራ መድረሱን ገልጸው፤ የዝርፊያው መጠን ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዝርፊያው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የገቡ የኤሌክትሪክ መሠረተ-ልማቶችን ላልተገባ ዓላማ ለማዋል የሚደረግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እየተፈፀመ ባለው ዝርፊያ ሳቢያም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ግሪዶች ደካማ እንዲሆኑ እና ሕብረተሰቡ በሚፈልገው መጠን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዳይደርሰው እያደረገ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
በተጨማሪም አገልግሎት ሰጪ የሆኑ ባንኮች፣ የሕክምናና ሌሎች ተቋማት በሚደርሰው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሳቢያ በሚፈለገው ልክ አገልግሎት መስጠት እየቻሉ አለመሆኑን አመልክተዋል።
ሥርቆቱ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሁሉም ክልሎች የሚደርስ መሆኑንም ነው አቶ ሞገስ ያነሱት።
በሥርቆቱ እየባከነ ያለውን ኃብት ለመተካት የሚወስደው ረዥም ጊዜም ሌሎች እየተካሄዱ ያሉ ልማቶች በታለመላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁም ጭምር እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሠረተ-ልማቱ ላይ የሚፈፀመው ሕገ-ወጥ ተግባር ከገንዘብ ኪሳራ ባለፈ በርካታ ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይም ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ነው ያሳሰቡት።
በአሁኑ ወቅትም በፈጻሚዎች ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃ ከሚደርሰው ጉዳት ጋር ተመጣጣኝ አለመሆኑም ለችግሩ መባባስ እንደምክንያትነት የሚጠቀስ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡም የሚደርሰውን ችግር ለመቅረፍ በአካባቢው ያለውን መሠረተ-ልማት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል