በመዲናዋ የመማር ማስተማር ሥራውን ሲያውኩ የተገኙ ከ 2 ሺህ በላይ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የመማር ማስተማር ሥራውን ሲያውኩ የተገኙ ከ 2 ሺህ በላይ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወስዷል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 14/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ ባለፉት ስምንት ወራት የመማር ማስተማር ሥራውን ሲያውኩ የተገኙ ከ2 ሺህ በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወንድሙ ዑመር ለኢዜአ እንዳሉት፤ ትምህርት ቤቶች ከአዋኪ ድርጊቶች ነፃ በማድረግ ምቹ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር እየተሰራ ነው።
በ2015 በጀት ዓመት በተደረገ የዳሰሳ ጥናት በርካታ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሥራውን በሚያውኩ ድርጊቶች ስጋት ሥር መሆናቸውን መለየት ተችሏል ብለዋል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ መሠረት ጥቂት በማይባሉ ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የአደንዛዥ ዕፅ መጠቀሚያ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ፔንሲዮኖችና ቁማር ቤቶች መኖራቸው ተረጋግጧል ነው ያሉት፡፡
እነዚህ ድርጊቶች ደግሞ አንዳንድ ተማሪዎች የመማር ፍላጎታቸው እንዲቀንስና በሱስ እንዲጠመዱ እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ድርጊቶቹ በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደሩ በመሆኑ ይህንንም ለማስቀረት ግብረ-ኃይል ተቋቁሞ በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን አመላክተዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ስምንት ወራት የመማር ማስተማር ሥራውን ሲያውኩ በተገኙ 2 ሺህ 6 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልፀዋል፡፡
በቀጣይም ይህ ድርጊት በመዲናዋ ባሉ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ እስኪወገድ ድረስ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፤ የመማር ማስተማር ሥራውን ይበልጥ ምቹ ለማድረግ የትምህርት ማኅበረሰቡ የስነ-ምግባር መመሪያ ሪፎርም በማዘጋጀት ወደ ሥራ እንዲገባ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ሪፎርሙ በተለይ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ግቢ የሚከለከሉና የሚፈቀዱ ጉዳዩች ላይ ግንዛቤ የሚሰጡ ነጥቦች መካተታቸውን አመላክተዋል።
በተለይ የመማር ማስተማር ሥራውን በሚያውኩ ድርጊቶች ላይ የትምህርት ቢሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመዲናዋ ከ 2 ሺህ በላይ የመንግሥት እና የግል ትምህርት ቤቶች እንደሚገኙ ይታወቃል።