በኦሮሚያ ክልል የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩ ህይወት እንዲሻሻል ዕድል ፈጥሯል - አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ

255

ሮቤ ፤ መጋቢት 14/2016(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ለአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥና የሥራ ዕድልም መፈጠሩን በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አብዱልሀኪም ሙሉ ገለጹ። 

የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በባሌ ዞን የተለያዩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል።

የስራ ኃላፊዎቹ በዞኑ ዲንሾና ጎባ ወረዳዎች በተለይ በተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ጥበቃ ሥራ የተገኙ ውጤቶችን ጎብኝተዋል።

አቶ አብዱልሀኪም እንዳሉት በክልሉ እየተከናወነ ያለው የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማትና ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የሥራ ዕድል ምንጭ እየሆነ መጥቷል።

በተፈጥሮ ኃብት ልማት ሥራ ከዚህ በፊት በሰው ሰራሽ ተፅዕኖ ምክንያት ተራቁተው ከአገልግሎት ውጪ የነበሩ አካባቢዎች ተከልለው እንዲያገግሙ በማድረግ ዳግም ለልማት እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

በተለይ በወረዳዎቹ ከዚህ በፊት ደን ተመንጥሮ የተራቆተ ተራራ ዳግም በማልማት ወጣቶችን በማደራጀት በንብ ማነብ ስራ እንዲሰማሩ መደረጉ ትልቅ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

አቶ አብዱልሀኪም እንዳሉት፣ የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ሥራ ይበልጥ የሥራ ዕድል ምንጭ እንዲሆን ህብረተሰቡና በየደረጃው የሚገኙ የአመራር አባላት የተጀመረውን ሥራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስቧል። 

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፣ በዞኑ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ጥበቃ ሥራ የአርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው። 

በዞኑ በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ230 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ዝሪያ ያላቸው ችግኞች እየተዘጋጁ መሆኑንም አመልክተዋል። 

በዞኑ በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ሥራ 88 ሺህ ሄክታር መሬት የሚያካልል የተቀናጀ የተፈጥሮ ኃብት ልማት ሥራ በዘመቻ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ ናቸው። 

በዘመቻው የእርከን ሥራ፣ ውኃን የሚያስተላልፉ መስመር፣ ውኃን የሚያቁሩ ስፍራዎች እየተከናወኑ ሲሆን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል። 

ከዲንሾ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር መሐመድ አብደላ በሰጡት አስተያየት፤ ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው ባከናወኑት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ ውጤት ማየት ጀምረዋል። 

በተለይ የተራቆቱ አካባቢዎችን በችግኝ በመሸፈንና መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ ለምርታማነታቸው መሻሻል አስተዋጽኦ እያደረጉ መምጣታቸውን ተናግረዋል። 

ባለፉት ዓመታት ያለሙት ተፋሰስ መልሶ በማገገሙ የዘንድሮው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በንቃት ማከናወናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የወረዳው ነዋሪ አበባ ከተማ ናቸው። 

''የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ መስራት ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ አድርገን ይዘናል'' ብለዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም