በክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሆሳዕና ፤ መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ የሕዳሴው ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ለግድቡ ግንባታ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ መቻሉንም ተመላክቷል።
ጽህፈት ቤቱ የግድቡ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 13ኛ ዓመት ክብረ በዓል አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
የክልሉ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽህፈቱ ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ አሼቦ በእዚህ ወቅት እንዳሉት፣ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከክልሉ በዓይነትና በገንዘብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ለዚህም ጽህፈት ቤቱ የተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ መንገዶችን በመቅረጽ የተጠናከረ ሥራ እየሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
የግድቡን 13ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት የኪነ ጥበብና ሌሎች መርሃግብሮች መዘጋጀታቸውን ጠቁመው፣ በዚህም ለግድቡ ግንባታ ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዷል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት በክልሉ ለሕዳሴው ግድብ ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ለማሰባሰብ ታቅዶ ባለፉት ሰባት ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ግድቡ የህዝቦች አንድነትና የልማት ቁጭት የታየበት መሆኑን ያነሱት ሃላፊው፣ የክልሉ ህዝብ ግድቡ ተጠናቅቆ ለታለመለት ዓላማ እስኪውል ድረስ ድጋፉን ያጠናክራል ብለዋል።
ዘንድሮ ለማሰባሰብ የታቀደውን ገንዘብ ለማሳካትም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች የቦንድ ሽያጭና መሰል የገቢ ማሰባሰቢያ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ሲሉም አስረድተዋል።
አቶ ተክሌ እንዳሉት የግድቡ መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦትን በማሳደግ ሀገራዊ ልማትን ለማፋጠንና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
ግንባታው እንዲጠናቀቅ የሁሉም ዜጋ ያልተቆጠበ ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ በክልሉ የህብረተሰቡን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ለግድቡ የሚደረግ ድጋፍ የዜጎችን ህብረትና የልማት ትብብር ከማጠናከር ባለፈ የቁጠባ ባህልን ማሳደጉንም አስታውሰዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕዳሴው ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ ከ410 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።