ቀጥታ፡

የተሰጠን የማዕረግ ዕድገት ለተጨማሪ ግዳጅና አገልግሎት የሚያነሳሳ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦  የተሰጣቸው የማዕረግ ዕድገት ለተጨማሪ ግዳጅና አገልግሎት የሚያነሳሳቸው መሆኑን የማዕረግ ዕድገት ያገኙ የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ተናገሩ።

የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በሥራ አፈፃፀማቸው ውጤታማ ለሆኑና የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ሰጥተዋል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የማዕረግ ተሸላሚ ከፍተኛ መኮንኖች፤ ለረጅም ዓመታት የሰሩበት አየር ኃይል ተቋማዊ ቁመናው ባደገበት ጊዜ ዕድገት ማግኘታቸው እንዳስደሰታቸው ጠቁመዋል። 

ከ30 ዓመታት በላይ በሠራዊቱ ውስጥ ያገለገሉት ኮሎኔል ሽብሩ ተስፋዬ፤ አየር ኃይል የደረሰበት የቴክኖሎጂ አቅምና ተቋማዊ ገጽታ ኢትዮጵያዊያን የሚመኙት እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚህ ወቅት ማዕረግ ማግኘታቸው እራሳቸውን እንደ ዕድለኛ አድርገው እንደሚቆጥሩት ገልፀዋል።

ያገኙት ማዕረግም ሌሎች ተቋሙን የሚቀላቀሉ አባላትን ለመቅረጽና አገርን ለማገልገል አዲስ ኃላፊነት የሚወስዱበት እንደሆነ አንስተዋል።


 

በአየር ኃይሉ የሦስተኛ ምድብ አዛዥ ኮሎኔል ደረጀ ቡሸራ በበኩላቸው የማዕረግ ዕድገቱ ተጨማሪ ተልዕኮና ግዳጅ ለመወጣት የሞራል ስንቅ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ቀደምት አባቶች ደማቅ ታሪክ ፅፈው ኢትዮጵያን እንዳስረከቡት እኛም በተግባር ከተናጋሪ ወደ ታሪክ ሰሪነት መሸጋገር አለብን፤ ለዚህም በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።  

ወጣቶችም አየር ኃይልን በመቀላቀል አገራቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

ከሌሎች የማዕረግ ተሸላሚዎች መካከል በዕለቱ የኮሎኔል ማዕረግ የለበሱት ብቸኛዋ ሴት ኮሎኔል አበበች ተሾመና ሌተናል ኮሎኔል ደሳለኝ ጌጡ፤ የማዕረግ ዕድገት ለተጨማሪ ግዳጅና አገልግሎት የሚጋብዝ መሆኑን ጠቅሰዋል። 


 

ያም ብቻ ሳይሆን አገራቸውን በቅንነት፣ በታማኝነትና በጀግንነት ለማገልገል እንዲዘጋጁ ስንቅ እንደሚሆናቸው ጠቁመዋል። 


 

ሌላው የማዕረግ ተሸላሚ ሻለቃ ተላሶን ዳንኤል፤ ከአባቶች በወረሱት ጀግንነትና የአገር ፍቅር ስሜት በመመራት ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማውረስ እንሰራለን ብለዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም