በባህር በር ዙሪያ በየደረጃው የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ያስችላሉ- የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት - ኢዜአ አማርኛ
በባህር በር ዙሪያ በየደረጃው የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ያስችላሉ- የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት
ነቀምቴ ፤ መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ)፡- በባህር በር ዙሪያ በየደረጃው የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ የሚያግዙ መሆናቸውን የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተናገሩ።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ አመራርና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ''የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ፣ ለኢኮኖሚ፣ ታሪክና ህጋዊ አግባብ'' በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት አካሄዷል።
የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሀሰን የሱፍ፣ በዚሁ ወቅት ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ በሰጥቶ መቀበል መርህ በመሆኑ ይደገፋል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የባህር በር ጥያቄው የአገሪቷን ልማትና እድገት ለማረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው በዚህ ረገድ የሚጠበቅበትን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
ይህ ጉዳይ የሀገራችን እና ትውልዱ ተስፋ ስለሆነ አስፈላጊነቱን በማስገንዘብ ረገድ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ሚናቸውን መወጣት አለባቸው ነው ያሉት።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም የሀገር ግንባታ ስራ ያለ ምሁራን ተሳትፎ የማይታሰብ በመሆኑ ምሁራን ባላቸው እውቀት እና ልምድ ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል።
በተለይም ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ በባህር በር ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች የጋራ ግንዛቤ ለመያዝ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ደምስ ፈረዲሳ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም ባህር በር የአንድን አገር ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማሲ አቅም የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያም እያደገ የመጣውን ኢኮሚያዋን የበለጠ ለማጠናከርና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ጥያቄውን ማንሳቷ ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል።
የባህር በር ጥያቄው ውጤት እንዲያመጣ መንግስት ከሚያደርግው እንቅስቃሴ ጎን ለጎን ምሁራንም ጥያቄውን በጥናትና ምርምር ማገዝ አለባቸው ብለዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አስፍው ቀኖ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ያቀረበችው የባህር በር ጥያቄ ዓለም ዓቀፍ ህግን ታሳቢ ያደረገ ነው ይላሉ።
ይህ ጥያቄ በሁሉም መልኩ ተቀባይነት ያለው እና አስፈላገነቱም ለሁሉም በመሆኑ በተለይ ምሁራን በዚህ ረገድ ድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።