ቀጥታ፡

የውኃ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የውኃ ኃብት አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር ይገባል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የውኃ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የውኃ ኃብት አስተዳደር ሥርዓትን በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም በቴክኖሎጂ ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ። 

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ውኃ አስተዳደርና ልህቀት ማዕከል የዓለም የውኃ ቀንን ምክንያት በማድረግ አውደ ጥናት አካሂዷል።  

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) "ውኃ ለብልጽግናና ሠላም" በሚል ርዕስ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል።

በገለጻቸውም፤ በኢትዮጵያ ውሃን በአግባቡ የማዳረስ ጥረቱ በበርካታ ፈተናዎች የታጀበ ነው ብለዋል።   

ከፈተናዎቹ አንዱ የውኃ አቅርቦት እጥረት መሆኑን ጠቁመው የአቅርቦት ችግሩን ለመፍታት የተሻለ የውኃ ኃብት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት ይገባል ብለዋል።    

ለዚህም በዘርፉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ፣ የሰለጠነ ሰው ኃይል መመደብና በቂ የፋይናንስ ኃብት ፈሰስ በማድረግ ረገድ ብዙ መሥራት ይገባል ነው ያሉት።     

በዘርፉ በቂ የሰው ኃይል ከሌለ፣ ቴክኖሎጂን በሚፈለገው መጠን መጠቀም ካልተቻለ፣ በቂ መሰረተ ልማት ካልተዘረጋ በውኃ አጠቃቀምና አስተዳደር ለውጥ ማምጣት አይቻልም ብለዋል። 

ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ለውኃ ኃብት አስተዳደር ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመው በአመራር ደረጃም በቁርጠኝነት ሊሰራበት እንደሚገባም አጽንዖት ሰጥተዋል።      

የዝናብ፣ የጎርፍና የምንጭ ውኃን ተገቢው ሕክምና በማድረግ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንዲሁም በግድቦችና በሌሎች አማራጮች ውኃን መያዝና በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የውኃ  አቅርቦት እጥረት ችግሩን ለመፍታት ትልቅ ሚና እንዳለውም አስረድተዋል። 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ውኃ አስተዳደርና ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ዘለቀ ዘውገ በበኩላቸው ማዕከሉ በውሃው ዘርፍ ብቁ የሰው ሃይል ማፍራት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በመስኩ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ኃሳቦችን ማፍለቅ ሌላው የማዕከሉ ኃላፊነት መሆኑን ጠቁመው ማዕከሉ በዚህም ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም