አየር ኃይልን በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
አየር ኃይልን በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ የማደራጀት ተግባራት ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ አየር ኃይል በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በትጥቅና በቴክኖሎጂ ይበልጥ የማደራጀት ተግባራት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሥራ አፈፃፀማቸው ውጤታማ ለሆኑና የመቆያ ጊዜያቸውን ለሸፈኑ ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ እድገት ሰጥቷል።
የማዕረግ እድገት የተሰጣቸው ባለፈው ዓመታት ለተቋሙ ሁለንተናዊ ለውጥ የራሳቸውን አበርክቶ ያደረጉ አባላት እንደሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ለከፍተኛ መኮንኖቹ ማዕረጉን ሰጥተዋል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዡ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ጠንካራ አየር ኃይል መገንባቷን ተናግረዋል።
የተያዘው በጀት ዓመት አየር ኃይል ዘመናዊ ትጥቆችን ያሟላበትና ሠፊ መሰረት ልማት ያከናወነበት ዓመት ነው ብለዋል።
ዓመቱ ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የደረሰችበትን ከፍታ የታየበት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዓለም በደረሰበት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚመሩና የነገ አየር ኃይል መሪ የሰራዊቱ አባላት የተመረቁበት ዓመት መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህ ተቋማዊ ለውጥ የሚመጣውም በአመራሮችና የሰራዊቱ አባላት የጋራ ሥራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ የአየር ኃይል ተቋም የሚገነባው አገርና ሕዝብ በሰላም እንዲኖር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚናፍቁ ጠላቶች እንቅልፍ ስለማይተኙ ሰራዊቱ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ብለዋል።
የተቋሙ መሰረታዊ ሪፎርም፤ ለታላቅ አገር ታላቅ ሠራዊት ግንባታ በመሆኑ በሰው ኃይል ልማት፣ በትጥቅና ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተጠናከረ ይቀጥላል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይወዱ ጠላቶች በየቦታው የሚፈለፍሏቸው ጽንፈኛ ኃይሎች በሰራዊቱ ብርቱ ክንድ ተደቁሰው ለአገር ሥጋት በማይሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል ብለዋል።