ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራው መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል ቅንጅታዊ ሥራው መጠናከር እንዳለበት ተገለጸ
ሀዋሳ፤ መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ) ፦ ህገወጥ የምግብና የመድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል በቅንጅት የተጀመረው ሥራ መጠናከር እንዳለበት በዘርፉ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት ገለጹ።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ከተለያዩ ክልሎች ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር በሻሸመኔ የምክክር መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላት ለኢዜአ እንደገለጹት ህገወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል ቅንጅታዊ አሰራርን ማጠናከር አስፈላጊ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊና የጤናና ጤና ነክ አገልግሎቶች ግብአት ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ አለሙ በክልሉ ህገ ወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ባለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ከሚገኙ 501 የመድሃኒት መደብሮች በ136ቱ ቁጥጥር ተደርጎ ከ45 በላይ ህገወጥ መድሃኒቶች ሲሸጡ ተገኝተው መወረሳቸውን ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ በጥፋቱ የተሳተፈ አንድ መድሃኒት ቤት ሙሉ በሙሉ ፈቃዱ መሰረዙንና ለዘጠኙ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ከምግብ ጋር በተያያዘም 445 ሺህ ብር የሚያወጣ ከደረጃ በታች የሆነ የምግብ ምርት ማስወገዳቸውንም ጠቅሰዋል።
በሃላባና ሆሳዕና ከተሞች ትምባሆን ለመከላከል የተጀመረውን ስራ በሌሎች ከተሞች ለማስፋት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የሲዳማ ክልል ጤናና ጤና ነክ ግብአት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቡሪሶ ቡላሾ በበኩላቸው "በህገወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውር መከላከል ሥራ ህብረተሰቡን የቁጥጥሩ አካል ማድረግ ይገባል" ብለዋል።
በክልሉ ህገ ወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውርን ለመከላከል በቅንጀት በተሰራው ስራ ከ13 በላይ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ህጋዊ ሂደቱን ተከትለው ውሳኔ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ባለስልጣኑ ከፍትህ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ ሥራ ጠንካራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ህገወጥ ዝውውሩን በመከላከል የህብረተሰቡን ደህንነት ለማስጠበቅ በቅንጅት የተጀመረው ሥራ መጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ህገወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውር በሰው ህይወትና ጤና ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በማስመልከት ያገኙት ግንዛቤ ለቀጣይ ሥራቸው አጋዥ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካሶ ናቸው።
በዘርፉ የሚከናወኑ ህገወጥ ተግባራትን በዘላቂነት ለመከላከል የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ውስጥ በማካተት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በሃዋሳ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የኮንትሮባንድ መከላከል አስተባባሪ ኮማንደር መቻል ተኮላ በበኩላቸው በጉምሩክ መቆጣጣሪያ ጣቢያዎች በርካታ ህገወጥ ምግቦች፣ መድሃኒቶችና ውበት መጠበቂያዎች እንደሚያዙ ገልጸዋል።
ችግሩ በማህበረሰቡ ላይ ከሚያስከትለው ጫና አንጻር ቅንጅታዊ ሥራው ጠንካራ እንዳልሆነ ገልጸው፣ በቀጣይ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፍቃዱ ንማኔ የውይይት መድረኩ በህገወጥ ምግብና መድሃኒት ዝውውር ቁጥጥር ላይ የባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ በማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ለማጠናከር የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ በአምስት ክልሎች ለሚገኙ ከ412 በላይ የምግብና መድሃኒት አስመጪዎች፣ አከፋፋዮችና አምራቾች ፈቃድ ሰጥቶ ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የቁጥጥር ሥራው ከበርካታ ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፣ "ህገወጥ ዝውውርን ለመከላከል በርካታ ሥራዎች ቢሰሩም ከችግሩ ስፋት አንጻሩ ቅንጅቱን ማጠናከር ይገባል" ብለዋል።
በመድረኩ የምግብና አስተዳደር አዋጅን ጨምሮ የቁጥጥር ዘርፉ ዋና ዓላማ ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ተደርጓል ።
በመድረኩ የፍትህ አካላት፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ የጤና ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።