ቀጥታ፡

የንግድና ኢንቨስትመንት አቅምን ለማጎልበት ጥራት ያለው የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሥርዓት መከተል ያስፈልጋል - ብሩክ ታዬ  (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ የንግድና ኢንቨስትመንት አቅምን ለማጎልበት በጥራት ላይ የተመሰረተ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሥርዓት መከተል እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ከፓን አፍሪካ የሂሳብ አዋቂዎች ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያካሄደው አህጉራዊ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ጥራት ማረጋገጫ አውደ ጥናት ዛሬ ተጠናቋል። 

ከመጋቢት 10 እስከ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው አውደ ጥናት የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድ የስራ ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ሀገራትን የወከሉ የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች ተሳትፈዋል። 

በዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፥ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ጥራት ቁጥጥር አውደ ጥናት ወጥ የሆነ አህጉራዊ አሰራር ለመዘርጋት ያግዛል ብለዋል።

በጤናማ የቁጥር መግለጫ ላይ የተመሰረተ የሂሳብ አያያዝና የኦዲት አሰራር መከተል የአፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።

ጥራት ያለው የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ድርጅቶች ገቢና ወጪያቸውን በግልጸኝነት እንዲያስተዳድሩና የፋይናንስ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።

የካፒታል ዕድገት የሚፈልግ ማንኛውም ድርጅት ወይም ግለሰብ ንግድና ኢንቨስትመንቱን ለማሳደግ በጥራት ላይ የተመሰረተ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ሥርዓትን መከተል እንዳለበት አስገንዝበዋል።


 

የኢትዮጵያ ሂሳብ አያያዝ እና ኦዲት ቦርድ ዋና ዳይሬክተር ሂክመት አብደላ በአውደ ጥናቱ የ25 አፍሪካ ሀገራት የሂሳብ አያያዝና ኦዲት መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና ሙያተኞች ተሳትፈዋል ብለዋል።

የምክክር መድረኩም ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን የተከተለ አህጉራዊ የኦዲት ሥርዓትን በመዘርጋት የአፍሪካን ንግድና ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ዓላማ ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ቦርዱ ባለፈባቸው ስምንት ዓመታት የዕውቀት ማነስና ብቁ የሰው ሃይል እጥረት በኦዲት ጥራት ክትትል የስራ ክፍል ላይ ጫና አሳድሮ መቆየቱን ገልጸዋል።

በዚህ መነሻ የውጭ ሀገራት የኦዲት ጥራት ክትትል አማካሪ በመቅጠር የኦዲተር ፈቃድ በመስጠት የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በጥራት ላይ የተመሰረተ የኦዲት ፋይናንስ ስርዓት መከተል ለአንድ ሀገርና ድርጅት ጤናማ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በኢትዮጵያም ጥራት ያለው የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ስርዓት ለመዘርጋት ከብሔራዊ ባንክ፣ ከካፒታል ማርኬት እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በትኩረት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የፓን አፍሪካ የአካውንታንቶች ፌዴሬሽን የጥራት አማካሪ ቡድን ሊቀ-መንበር ጆርጅ ሞኩአ፥ ወጥ የሆነ አህጉራዊ የኦዲት ሥርዓትን መዘርጋት የአውደ ጥናቱ ዋና ዓላማ ነው ብለዋል።

በጥራት ላይ የተመሰረተ ዓለም አቀፋዊ የኦዲት አሰራርን መከተልም በአህጉራዊ የንግድ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲጣልበት እንደሚያደርግ ገልጸዋል። 

አውደ ጥናቱ የአፍሪካ ሀገራት በሂሳብ አያያዝና ኦዲት ስራዎች ላይ የሚያጋጥሟቸውን የጥራት ችግሮች በማስተካከል የጋራ መፍትሔ ለመስጠት ያስችላል ሲሉ ተገጸዋል።

ለአራት ተከታታይ ቀናት በቆየው አውደ ጥናት ላይ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሂሳብ አያያዝና ኦዲት ጥራትን ማሳደግና ማረጋገጥ የሚያስችሉ የመነሻ ጽሁፎች ቀርበው ምክክር ተካሂዶባቸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም