ቀጥታ፡

በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናያውን በባለቤትነት የሚተሳተፉበት አፍሪካ መር ውይይት ያስፈልጋል- አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናያውን በባለቤትነት የሚተሳተፉበት አፍሪካ መር ፣ ሁሉን አቀፍ እና አካታች ውይይት እንደሚያስፈልግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በአፍሪካ ሕብረት ማዕቀፍ በሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት የተዋቀረውን የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ፓናል ቡድን አባላትን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። 


 

አምባሳደር ታዬ በሱዳን ያለውን ግጭት ለመፍታት ሱዳናያውን በባለቤትነት የተሳተፉበት እና በአፍሪካ ህብረት የሚመራው ሁሉን አቀፍ እና አካታች ውይይት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

በተለይም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ስር የሚከናወኑ የሰላም አማራጮችን ማጠናከር እንደሚገባም በውይይቱ ወቅት አንስተዋል። 

አምባሳደር ታዬ በሱዳን የተፈጠረው ችግር ለመፍታት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ለተዋቀረው የሱዳን ፓናል ኢትዮጵያ ደስተኛ መሆኗን እና የምትችለውን ድጋፍ ሁሉ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።

የተዋቀረው ቡድን ሊቀመንበር ሙሀመድ ኢብን ቻምባስ በበኩላቸው በግጭቱ ምክንያት ለተፈጠረው የሰብዓዊ ቀውስና ተያያዥ ችግሮች አፋጣኝ ምላሽ እንደሚያስፈልገው ገልጸዋል። 

ሊቀመንበሩ በሱዳን ሰላም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የአፍሪካ ህብረት የሱዳን ከፍተኛ ፓናል በህብረቱ ሳይለንስ ዘገን ልዩ ልዑክ በሆኑት ሙሃመድ ቻምባስ የሚመራ ሲሆን የኡጋንዳ የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ሰፔሊኦዛ ካዚኮዌ እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት የሱማሊያ ልዩ ተወካይ አምባሳደር ፍራሲስኮ ማድራን በአባልነት ያቀፈ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመረጃው አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም