የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለመሰረተ ልማት ግንባታ የሰጠው ትኩረት የሚበረታታ ነው -- ወይዘሮ ጫልቱ 

ባህርዳር፤ መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ)፦ የባህርዳር ከተማን በዘመናዊ የመሰረተ ልማት ግንባታ በማስተሳሰር፣ ለቱሪዝምና ለነዋሪዎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።

በሚኒስትሯ የተመራው የፌዴራል መንግስት የድጋፍና ክትትል ቡድን በባህርዳር ከተማ የ4 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አዲስ የጠጠር መንገድ ግንባታ አስጀምረዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት በከተሞች የሚከናወኑ የመሰረተ ልማት ግንባታ የወደፊት የህዝብ ቁጥርና እድገትን መሰረት ያደረገና ዘላቂ መሆን አለበት።


 

የመንገድ መሰረተ ልማት መስፋፋት የሀገር ኢኮኖሚን ከማጠናከር ባሻገር የዜጎችን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትስስር ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የባህርዳር ዳር ከተማ አስተዳደርም ይሄን በመገንዘብ በያዝነው ዓመት ከሰላም ማስከበር ጎን ለጎን የተለያዩ የመሰረተ ልማት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ የሚበረታታ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቶቹ የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡና በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ጎሹ እንዳላማው በበኩላቸው ባህርዳርን ፅዱ፣ ውብና ሳቢ፣ ለነዋሪዎች ምቹና በጎብኚዎች ተመራጭ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አሁን ላይ በአምስት ክፍለ ከተሞች የውሃ ማፋሰሻ የተሟላላቸውና በቀጣይ ወደ ጌጠኛ ድንጋይና አስፋልት ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ የጠጠር መንገዶች ግንባታ መጀመሩን ተናግረዋል።

ለነባርና ዘንድሮ ለሚጀመሩ 11 ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ናቸው።


 

ከዚህ ውስጥም የ93 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በተለያዩ ክፍለ ከተሞች በአዲስ መልክ ግንባታቸው  ለተጀመሩት የ4 ነጥብ 5  ኪሎ ሜትር  መንገዶች መሆኑን አመልክተዋል።

በከተማዋ የበላይ ዘለቀ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አሽዬ የኑስ በሰጡት አስተያየት ሰፈራቸው በክረምት ባጃጅና አምቡላንስ ለማስገባት ችግር እንደነበር ጠቁመው በመንገዱ መጀመር መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት የተጀመሩ የ22 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር የአስፓልት ግንባታ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የመንገድ ዳር መብራት ተከላና ሌሎች ስራዎች ግንባታም ተጠናክሮ መቀጠሉ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም