ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚቃጣበትን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም አለው - ኢመደአ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከውስጥም ይሁን ከውጪ የሚቃጣበትን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው ማረጋገጡን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ገለጸ። 

አስተዳደሩ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነትና ሉአላዊነት ለማረጋገጥ በጥንቃቄና በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈጠረውን ክስተት አስመልክተው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አስተዳደሩ ባደረገው ምርመራ ባንኩ ከውስጥም ይሁን ከውጪ የሚቃጡበትን የሳይበር ጥቃት አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል አቅም እንዳለው ማረጋገጣቸውን ገልጸዋል። 

ባንኩ አስፈላጊውን የሳይበር ደህንነት ጥንቃቄ እንደሚያደርግ በባንኩ ሲስተሞች ላይ የተደረገው ፍተሻ እንደሚያሳይም ተናግረዋል።

አስተዳደሩ በባንኩ ላይ ባደረገው የደህንነት ፍተሻና ምርመራ ችግሩ የተፈጠረው ከሲስተም ማሻሻያ ጋር በተገናኘ መሆኑን ማረጋገጡን ጠቅሰዋል።

የተፈጠረው ችግር የሳይበር ጥቃት መሆኑን የሚያሳይ ምንም አይነት መረጃ አለመገኘቱንም ጠቁመዋል።

በባንኩ ላይ ከውጪ የተቃጣ ምንም ዓይነት ጥቃት አለመኖሩን ጠቁመው ተጨማሪ የውስጥ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

አስተዳደሩ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት እና ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ያለዕረፍት ለ24 ሰዓት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አስታውቀዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም