አገልግሎቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ዙር 20 ሺህ የሚጠጉ ስማርት ቆጣሪዎችን መቀየሩን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ዙር 20 ሺህ የሚጠጉ ስማርት ቆጣሪዎችን መቀየሩን ገለጸ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በሁለት ዙር 20 ሺህ የሚጠጉ ስማርት ቆጣሪዎችን መቀየሩን አስታወቀ።
አገልግሎቱ ለተቋሙ ደንበኞች የሚሰጠውን አገልግሎት በማዘመን የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ፤ተቋሙ ከመጋቢት ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 2016 በሁለት ዙር 20 ሺህ የሚጠጉ ስማርት ቆጣሪዎችን ቀይሯል።
ስማርት የኤሌትሪክ ቆጣሪ" አገልግሎት የመጀመሪያው ዙር የፓይለት ፕሮግራም ከመጋቢት 2014 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መስከረም 30 ቀን 2016 በሙከራ ደረጃ በአዲስ አበባ ተግባራዊ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም በመጀመሪያ ዙር 5 ሺህ ስማርት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ለመቀየር ታቅዶ 4 ሺህ 531 ቆጣሪዎችን መቀየር መቻሉን ገልጸዋል።
ከጥቅምት 1 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ መጋቢት 2016 ዓ.ም በሁለተኛ ዙር በተከናወነ ስራ 45 ሺህ ቆጣሪዎች ለመቀየር አቅዶ አሁን ላይ 15 ሺህ 46 ስማርት ቆጣሪዎችን መቀየር መቻሉን ነው የገለጹት።
የስማርት ቆጣሪ የመቀየሩ ሥራ የሚከናወነው በዋናነት ለኢንዱስትሪ እና ኮሜርሻል ደንበኞች እንደሆነም ተናግረዋል።
ቆጣሪዎች ወደ ስማርት ቆጣሪ መቀየራቸው የቆጣሪ ንባብ ወደ ቤት መምጣት ሳይጠበቅ እንዲነበብና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሲቋረጥ ከማዕከል ሆኖ ችግሩን ለመለየት ያስችላል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ደንበኞች በቀላሉ በእጅ ስልካቸው አማካኝነት ወርሃዊ የፍጆታ ሂሳባቸውን እንዲያውቁ ያስችላል ብለዋል፡፡
በተለይም ከቆጣሪ ንባብ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስቀረትና የኃይል ስርቆትን ለመከላከል የሚያስችል መሆኑንም ገልጸዋል።
አገልግሎቱ በቀጣይ ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎችን ወደ ተግባር በማስገባት የኃይል ብክነትን ለመቀነስ የሚያስችለውን አሰራር እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የሁለተኛው ዙር የስማርት ቆጣሪ የመቀየር ስራ ሲጠናቀቅ በቀጣይ 600 ሺህ የሶስት ፌዝ ቆጣሪዎችን በስማርት ቆጣሪ የመቀየር ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።
እንዲሁም በሂደት የሁሉንም ደንበኞች ቆጣሪ በስማርት ቆጣሪ በመቀየር አገልግሎቱን የማዘመን እና ሌሎች አማራጮችን የመዘርጋት ስራ የሚከናወን ይሆናል።