ተቋሙ በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋሙ በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠየቀ
አዳማ ፤መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት እንዲሰጡት ጠየቀ።
ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በምርመራና በመፍትሔ ሃሳብ አፈፃፀሞች ዙሪያ ከፌዴራልና ከክልል የፍትህ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት አካሄዷል።
በኢትዮጵያ ህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ዋና እንባ ጠባቂ ዶክተር እንዳለ ሀይሌ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ የዜጎችን መብትና ነፃነት ማስከበር የሁሉም አካላት ኃላፊነት ሊሆን ይገባል።
የዜጎች መብትና ነፃነት በአግባቡ ከተከበረ ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዲሞክራሲን ለማረጋገጥ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል።
ተቋሙም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡለትን ቅሬታዎች ተቀብሎ በመመርመር የመፍትሄ ሃሳብ ያቀርባል ብለዋል።
ተቋሙ በአቤቱታ ቅበላ፣ በምርመራና የመፍትሔ ሀሳብ አፈፃፀምን በሚመለከት እያጋጠሙ ባሉ ተግዳሮቶች ዙሪያ ለፍትህ አካላት ግንዛቤ መስጫ መድረኩ ማስፈለጉን ጠቁመዋል።
መብትን በማስከበር ሂደት የሚያገጥሙ ተግዳሮቶችን ለይቶ መፍታት የሁሉም አካላት ድርሻ መሆኑን የጋራ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋምም የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት በዜጎች ላይ የአስተዳደር በደል እንዳይፈፅሙ አስቀድሞ ለመከላከል፣ ተፈፅሞ ሲገኝም በአፋጣኝ እንዲታረም የማድረግ ኃላፊነቱን ለመወጣት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።
በዚህ ሂደትም ተቋሙ በተለያየ መንገድ የሚደርሱትን ቅሬታዎች በማጣራት የሚያቀርበውን ምክረ ሀሳብ የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ ጠይቀዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ በበኩላቸው ዜጎች ከህግና ፍትህ ስርዓቱ ተጠቃሚ ስለመሆናቸው እስከታች ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ በዘርፉ እያጋጠሙ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ጠቋሚ ነው ብለዋል።
የፍትህ አካላት በዜጎች ላይ የሚደርሱ በደሎችን በእኔነትና በቁርጠኝነት መፍትሔ በመስጠት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።
ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አለሙ መግራ፣ ዜጎች የሚደርሱባቸውን ችግሮች መፍታት ተቀዳሚ ተግባር መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
ዜጎች ፍትህ እንዲያገኙ በሚሰራው ስራ የሚፈለገውን ውጤት ለማሳካት የህግ ምክር እንዲያገኙና በህግ ጉዳዮች ግንዛቤ ማስጨበጫው እስከ ማህበረሰቡ መውረድ እንዳለበትም ጠቁመዋል።
ሌላው የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ባልደረባ የሆኑት አቶ አብዬ ካሳሁን፣ በአስተዳደር በደሎች አፈታት ላይ መንግስትንና ህዝብን ማስማማት የሚችል አሰራር ላይ ማተኮር አስፈላጊ ነው ብለዋል።
የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም በየደረጃው መፈተሽ ያለባቸው አሰራሮችን ማጤን የዜጎችን በደልና ቅሬታ መቀነስ ያስችላል ሲሉም አክለዋል።