ጠንካራ የአየር ኃይል ተቋም የምንገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው- ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
ጠንካራ የአየር ኃይል ተቋም የምንገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው- ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ ጠንካራ አየር ኃይል የምንገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።
ለከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት የማልበስ ስነ- ስርዓት ዛሬ ተከናውኗል።
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ጠንካራ አየር ኃይል መገንባቷን ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት እንደ ሀገር ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት እንደሆነ ገልጸው፤ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ትጥቆችን ያሟላንበትና ሰፊ መሰረት ልማት ያከናወንበት ዓመት ነው ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር የአድዋ ድል መታሰቢያ መገንባቱ የኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ጨምሮ ህዝቡ ለሀገር ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያን መረጋጋት የማይወዱ ጠላቶች በየቦታው የሚፈለፍሏቸው ኃይሎች ትንኮሳ ቢያደርጉም፣ በሰራዊቱ የጀግንነት ተጋድሎ ለሀገራችን ስጋት በማይሆኑበት ደረጃ ደርሰዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ የደረሰችበትን ከፍታ በ88ኛው የአየር ኃይል የምስረታ በዓል ማሳየት መቻሉን አስታውሰው፣ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቁ የሰራዊቱ አባላት የተመረቁበት መሆኑን ገልፀዋል።
ይህ ተቋማዊ ለውጥ የሚመጣውም በአመራሮችና የሰራዊቱ አባላት የጋራ ስራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጠንካራ የአየር ኃይል ተቋም የሚገነባው ሀገርና ህዝብ በሰላም እንዲኖር ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያን ውድቀት የሚናፍቁ ጠላቶች እንቅልፍ ስለማይተኙ ሰራዊቱ ሁልጊዜም ዝግጁ ነው ብለዋል።
የተቋሙ መሰረታዊ ሪፎርም፤ ለታላቅ ሀገር ታላቅ ሰራዊት ግንባታ በመሆኑ በሰው ኃይል ልማት፣ በትጥቅና ቴክኖሎጂ ይበልጥ እየተጠናከረ ይቀጥላል ነው ያሉት።