ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለተከታታይ ስምንት አመታት ከወር ደሞዜ ተቆራጭ በማድረግ በ184 ሺህ ብር ቦንደ ገዝቻለው- አቶ ኪሮስ አስፋው - ኢዜአ አማርኛ
ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለተከታታይ ስምንት አመታት ከወር ደሞዜ ተቆራጭ በማድረግ በ184 ሺህ ብር ቦንደ ገዝቻለው- አቶ ኪሮስ አስፋው
መቀሌ ፤ መጋቢት 13/2016 (ኢዜአ)፦ ለተከታታይ ስምንት አመታት ከወር ከደመወዛቸው ተቆራጭ በማድረግ በ184 ሺህ ብር ቦንደ የገዙት ኢትዮጵያዊ የግድቡ ግንባታ ለመጠናቀቅ በመቃረቡ መደሰታቸውን ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የተጀመረበትን 13ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ቃልን በተግባር ከገለፁት የልማት አርበኛ ጋር ቆይታ አድርጓል።
አቶ ኪሮስ አስፋው ይባላሉ። ነዋሪነታቸው በትግራይ ክልል ዓብይ ዓዲ ሲሆን "እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" የሚለው የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጭት አሁን እውን ሆኖ በማየታቸው ትልቅ ደስታ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
በዓብይ ዓዲ ሆስፒታል በጤና ባለሙያነት እያገለገሉ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ኪሮስ ከሚከፈላቸው ደሞዝ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ሳይሰለቹ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልፀዋል።
አቶ ኪሮስ እንዳሉት የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ አለማቋረጥ ለተከታታይ ስምንት ዓመታት ከወር ደመወዛቸው ተቆራጭ በማድረግ ቦንድ በመግዛት ትልቅ አሻራ ማኖራቸውን አውስተዋል።
ይህን ፅኑ እምነት መነሻ በማድረግ 184 ሺህ ብር ዋጋ ያለው በቁጥር 190 ቦንድ በመግዛት አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ለስምንት አመታት ያለማቋረጥ ቦንድ ለመግዛት ያነሳሳቸው "ኢትዮጵያ ስትለማ እኔም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ እሆናለሁ" ከሚል እሳቤ መሆኑን አቶ ኪሮስ ገልፀዋል።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲጀመር "እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን" የሚል የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጭት መኖሩን ያወሱት አቶ ኪሮስ እኔም የህዳሴ ግድብ ግንባታ ወደ ማጠናቀቁ ገደማ በመቃረቡ ቁጭቱ በተግባር እውን ሆኖ በማየቴ በጣም ደስተኛ ነኝ ብለዋል።
ግድቡን ለመጎብኘት በሄዱበት ወቅት አባይ ወንዝ አፋፍ ላይ በመድረስ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቦንድ እንደሚገዙ ቃል የገቡበትን ሁኔታ አስታውሰዋል።
ቃላቸውን በተግባር መንዝረውት እስከ 2013 ዓ.ም 102 ጊዜ አስተዋፅኦ በማድረግ የ184 ሺህ ብር ቦንድ ለመግዛት እንደቻሉ አስረድተዋል።