ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትልቅ ሚና ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ትልቅ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኃይማኖት አባቶችና ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይት ለዘላቂ ሠላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የላቀ ሚና እንዳለው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ካይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትር ዴኤታ ካይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ውይይቶቹ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታትና የተገኙ ድሎችን ለማስቀጠል መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው።
መንግሥት በተለይም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ያነሳበት በዚህም ዜጎች ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያመላከተ ጥልቅ ውይይት መሆኑንም ገልጸዋል።
ውይይቶቹ መንግሥት ለሕዝቡ የገባውን ቃል በምን መልኩ እየተገበረ መሆኑን ያስረዳበትና መንግሥት ባከናወናቸው ተግባራት ከሕዝቡ ምልከታና ግብዓት የሰበሰበበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህም ሕዝቡ መንግሥት በሚያከናውናቸው ተግባራት፤ በተለይም ደግሞ በሀገሪቱ ጉዳይ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል።
የዜጎች ኃሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ ባህል እየዳበረ መሄዱን ጠቁመው ይህም መንግሥት የዜጎችን ኃሳብ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚረዳውም ገልጸዋል።
ውይይቶቹ ለሠላም ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ለብሔራዊ መግባባትም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳላቸው አስረድተዋል።
መንግሥት ለሁሉም አካላት እኩል ዕድል ሰጥቶ መወያየቱ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት እንዲጠናከርና የአካታች የወል ትርክት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ጠቁመዋል።
መንግሥትና ኃይማኖት ለአገረ መንግሥት ግንባታ የየራሳቸው ሚና እንዳላቸው አንስተው የሁለቱ አካላት ተቀራርቦ መሥራት ለዘላቂና አዎንታዊ ሰላም ለመገንባት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በተለይም መንግሥት የኃይማኖት አባቶችን ጨምሮ ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር ያደረገው ውይይት በትብብር የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቱን ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፉት ጊዜያት ከሁሉም አካባቢዎች የማህበረሰብ ክፍሎችና ከሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ከተወጣጡ አባቶች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።