በውሀ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ትብብርን ማጠናከርና የጋራ አጠቃቀምን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦በውሀ ሃብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ትብብርን ማጠናከርና የጋራ አጠቃቀምን ማጎልበት እንደሚገባ ተጠቆመ።

የዓለም የውሀ ቀን "ውሀ ለሰላም" በሚል በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተከብሯል።

በአህጉራዊና ብሔራዊ ደረጃ የውሀ ሃብት አጠቃቀም፣ የውሀ ሀብት ላይ የተደቀኑ ችግሮች፣ ትብብርን ማጠናከርና ሌሎች የውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ትኩረት ያደረጉ  ጽህፎች ቀርበዋል።


 

የተቀናጀ የውሀ ሀብት አስተዳደር አስተባባሪ ዶክተር ብዙነህ አስፋው፤ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ለሰላምና ብልጽግና ያለው ፋይዳ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የውሃ ሀብትን የግጭት ምክንያት ከማድረግ ይልቅ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነትን በማጎልበት ለሰላምና ብልጽግና ማዋል እንደሚገባ በጽሁፋቸው አመላክተዋል።

በውሀ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ ትብብርን ማጠናከር፣ የጋራ አጠቃቀምን ማጎልበት፣ የውሀ ሃብትን የሚቀንሱ ችግሮችን በጋራ መፍታትና ሌሎች የትብብር ዘርፎችን ማጠናከር እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን የውሃ ሃብትን በዘላቂነት ለመጠቀም ብሔራዊ የተቀናጀ የውሀ ሃብት አጠቃቀም ስትራቴጂ ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም