ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ጥራትና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በላቦራቶሪ ፍተሻ እንዲያልፉ ይደረጋል-ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ጥራትና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በላቦራቶሪ ፍተሻ እንዲያልፉ ይደረጋል-ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 13/2016(ኢዜአ)፦ወደ ውጪ የሚላኩ የግብርና ምርቶች ጥራትና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ኤርፖርት በላቦራቶሪ ፍተሻ እንዲያልፉ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን አስታወቀ።
ኢትዮጵያ ከሆርቲካልቸር ዘርፉ የተሻለ ጥቅም የማግኘት ዕድል እንዳላት ተመላክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ድሪባ ኩማ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸው የግብርና ምርቶች ጥራታቸውን የጠበቁና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው ።
የግብርና ምርቶች በተለያዩ ተባዮች ጥራታቸው እንዳይጓደል ከእርሻ ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል ወደ ውጭ በሚላኩና ወደ ሀገር ውስጥ በሚገቡ ምርቶች ላይ ይደረግ የነበረው ቁጥጥር በተበታተነ መልኩ ይሰራ እንደነበር አስታውሰው፣ ባለስልጣኑ ይህን ስራ በባለቤትነት ለመስራት ከሁለት ዓመት በፊት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
ምርቶቹን በተመለከተ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ማጓጓዝ ባለው ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመለየት መፍትሄ ለሚሰጡ ባለሙያዎች ስልጠና እየተሰጠና የአሰራር ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የአውሮፓ ህብረት ኢትዮጵያን ጨምሮ ኬንያና አንዳንድ አበባ ላኪ የአፍሪካ ሀገራት ላይ እያጋጠመ የመጣውን ‘’የእሳት እራት’’ የተባለ ተባይ አስመልክቶ አዲስ ህግ አውጥቷል።
ቀደም ሲል ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት የሚገቡ የአበባ ምርቶች ላይ የሚደረገው የላብራቶሪ ቁጥጥር አምስት በመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን በአዲሱ ህግ መሰረት ቁጥጥሩ ወደ 25 በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል።
ይህን መስፈርት ያላሟሉ ሀገራት የአበባ ምርቶቻቸውን ወደ አውሮፓ እንዳያስገቡ እገዳ ጥሏል።
ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአንዳንድ አበባ እርሻዎች ላይ ያጋጠማትን የ’’የእሳት እራት’’ ተባይ ለማጥፋት ከእርሻ ጀምሮ ወደ ውጭ እስኪላክ ድረስ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል እያደረገች መሆኑን ነው አምባሳደር ድሪባ የሚናገሩት።
ይህ ተባይ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ኬንያን ጨምሮ በአንዳንድ አበባ ላኪ የአፍሪካ ሀገራት ላይ ያጋጠመ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ ተባዩን ለማጥፋት ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ መወሰዱን አንስተዋል።
በዚህም በዘርፉ ልምድ ካለው የኬንያ የቁጥጥር ተቋም ጋር ግንኙነት በመፍጠር አዲስ የቁጥጥር መመሪያ እንዲወጣ መደረጉን ተናግረዋል።
ምርታቸውን ወደ ውጭ የሚልኩ የአበባ እርሻ ኩባንያዎች በኬሚካልና በሌሎች ዘዴዎች ተባዩን እንዲያጠፉ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለሥልጣኑ በበኩሉ ከእርሻ ጀምሮ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ዘርፈ ብዙ ክትትል በማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ምርት ለመላክ የሚያስችል ቁጥጥር እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾችና ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴድሮስ ዘውዴ ኢትዮጵያ ከሆርቲካልቸር ዘርፉ የተሻለ ጥቅም የማግኘት ዕድል እንዳላት ተናግረዋል።
ምርቶችን ከእርሻ ጀምሮ ለገበያ እስኪቀርቡ ድረስ ጥራታቸውን የጠበቁና ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆን ማህበሩ የስልጠና ማዕከል ከፍቶ በየደረጃው ላሉ የዘርፉ ተዋንያን ስልጠና የሚሰጥ መሆኑንም ገልጸዋል።
ማህበሩ ጥራት ያለው ምርት እንዲመረትና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ነው ያነሱት።
ከዚህ ባለፈ ማህበሩ በዘርፉ ያሉ አሰራሮች እንዲስተካከሉና ለኢንዱስትሪው ምቹ የስራ ከባቢ መፍጠር የሚያስችሉ ህጎች እንዲወጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ 58 የአበባ እርሻዎች ያሉ ሲሆን እነዚህ እርሻዎች 80 በመቶ ምርታቸውን የሚልኩት ወደ አውሮፓ ነው።
በዚህም በዘርፉ በዓመት ከ500 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ አንደሚገኝ ማህበሩ ጠቅሷል።