ቀጥታ፡

በሚቀጥሉት 11 ቀናት በልግ አብቃይ  በሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ የዝናብ መጠን ያገኛሉ - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 12/2016 (ኢዜአ)፦ በሚቀጥሉት 11 ቀናት በልግ አብቃይ  በሆኑ አብዛኛው አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ  የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የቀጣዩን አስራ አንድ ቀናት ትንበያ አስመልክቶ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ በልግ አብቃይ  የሆኑ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ  የዝናብ መጠን ያገኛሉ።

በዚህም በኢትዮጵያ የሰሜን፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ፣ መካከለኛው፣ በሰሜን ምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆና አጎራባች አካባቢዎች ጠንከር ያለ የዝናብ ሁኔታ እንደሚኖር አመላክቷል።

አብዛኞቹ በልግ አብቃይ አካባቢዎችም ከቀላል እስከ መካከለኛ  መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ በመግለጫው አብራርቷል።

በመካከለኛው ሰሜን ምስራቅ እና የምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር መግለጫው አመልክቷል።

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም የወለጋና ሸዋ ዞኖች፣ ቡኖ በደሌ፣ ኢሉአባቦር፣ ጅማ፣ አርሲና ምዕራብ አርሲ፣ ባሌ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ጨምሮ የሐረሪ ክልል፣ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተሞች በአመዛኙ ከባድ ዝናብ እንደሚያገኙ አንስቷል።

የአማራ ክልል ደግሞ ምስራቅና ምዕራብ ጎጃም፣ የደቡብ፣ መካከለኛው እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች፣ ባሕር-ዳር ዙሪያ፣ የዋግህምራና ኦሮሚያ ልዩ ዞኖች፣ የሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖችም እንዲሁ በአንዳንድ ስፍራዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚስተዋል አስታውቋል።  

የአፋር ክልል ዞኖች፣ በትግራይ ክልል የደቡብ፣ ደቡብ ምስራቅ፣ ምስራቅ፣ መካከለኛው እና የሰሜን ምዕራብ የክልሉ ዞኖችም በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር አመላክቷል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና በሲዳማ ክልል ዞኖችም አንዲሁም በሱማሌ ክልልም እንዲሁ በሲቲና ፋፈን የተስፋፋ ዝናብ ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

በሌላ በኩልም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ፣ ጉጂና ምዕራብ ጉጂ፣ ቦረና፤ በትግራይ ክልል የምዕራብ ትግራይ ዞኖች፣ በሶማሌ ክልል የዳዋ፣ የሊበን፣ የአፍዴር፣ የኤረር እና የነጎብ ዞኖች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ  ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል።

በሚቀጥሉት 11 ቀናት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚስተዋለው ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው የዝናብ ሁኔታ የአርብቶ እና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች የግጦሽ ሳር እና የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በማሻሻል አይነተኛ ፋይዳ እንደሚኖረውም በመግለጫው ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም