ቀጥታ፡

የሰብአዊ ድጋፎችን በፍትሕዊነት በማሰራጨት ረገድ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል - የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ በመንግስት እየቀረቡ ያሉ ሰብአዊ ድጋፎችን በፍትሕዊነት በማሰራጨት ረገድ ክልሎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አሳሰበ።

በመንግስት መር አካሄድ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማስተባበር ለ6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ አታለል አቦሀይ፤ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍና ተደራሽነትን በተመለከተ ለኢዜአ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጠናከረ መልኩ እየቀረበ መሆኑንም ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በሦስት ዙሮች ጥሬ ገንዘብና አልሚ ምግቦችን ጨምሮ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ተደራሽ መደረጉን ተናግረዋል።

በዚህም ከ894 ሺህ ኩንታል በላይ እህል እና 540 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።

በአንደኛ እና ሁለተኛ ዙር ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ዜጎች የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል።

በሦስተኛ ዙር ደግሞ ለ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ የቀረበ ሲሆን፤ በሦስቱም ዙሮች በአጠቃላይ የ15 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር የዓይነትና የጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል።

የሰብአዊ ድጋፉ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግሮች ድጋፍ ለሚሹ የአፋር፣ ትግራይ እና አማራ ክልሎች ነዋሪዎች የቀረበ መሆኑንም አንስተዋል።

መንግሥት ሰብአዊ ድጋፍ አቋርጠው የወጡ ለጋሽ ድርጅቶች የፈጠሩትን ክፍተት ለመሙላት ከመጠባበቂያ የምግብ መጋዘኖች 894 ሺህ 302 ኩንታል እህል ድጋፍ ማቅረቡንም ጠቅሰዋል።

ዓለም አቀፍ አጋር ድርጅቶች ሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦቱን አቋርጠው እንደነበር አስታውሰው፤ በዲፕሎማሲያዊ ንግግር በመንግሥት መር አካሄድ ድጋፋቸውን እንዲቀጥሉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።  

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና በኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች የዲፕሎማሲ ሥራ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥምረት በ3ኛው ዙር ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች በ3ኛው ዙር 30 በመቶ የሚሆን የ400 ሺህ ኩንታል የሰብአዊ ድጋፍ መቅረቡን ጠቅሰው፤ ድጋፉ በ4ኛው ዙርም መቀጠሉን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መንግሥት መር የሆነውን የሰብዓዊ ድጋፍ አካሄድና መመሪያ እንዲከተሉ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲቀጥሉ እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።

በዚህም መንግሥት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችን በማስተባበር በ4ኛው ዙር ለ6 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያቀረበ ነው ብለዋል።

በመሆኑም የሚቀርቡ ድጋፎችን በፍትሃዊነት በማሠራጨት ክልሎች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ለጋሽ ድርጅቶችና ባለሃብቶችም ሰብአዊ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም