ቀጥታ፡

የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት አካባቢውን በልማት ለማስተሳሰር የሚያግዝ ነው- ዶክተር ጌድዮን

ጎንደር፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በጣና ሃይቅ ዳርቻ የሚገነባው የጎርጎራ ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት በአካባቢው ተጨማሪ ሃብት ለማመንጨትና ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል እንደሆነ የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ተናገሩ፡፡

በፍትህ ሚኒስትሩ የተመራው የፌዴራል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሱፐርቪዥን ቡድን ምልከታ ካደረገባቸው ፕሮጀክቶች መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ሃሳብ አመንጪነት ከሚከናወኑ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች መካከል የጎርጎራ ፕሮጀክት አንዱ ነው።

የሱፐርቪዥን ቡድኑ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የተከናወኑ የሰላም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ዛሬ ገምግሟል፡፡

የሱፐርቪዥን ቡድኑን የመሩት የፍትህ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጤሞቲዎስ በግምገማ መድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የጎርጎራ ፕሮጀክት የማዕከላዊ ጎንደርና ጎንደር ከተማን በማስተሳሰርና የቱሪስት ፍሰቱን በመጨመር ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ለጎርጎራ ከተማና ለአካባቢው አዲስ የመልማትና የማደግ ጸጋን ይዞ የመጣ በመሆኑ የከተማውን ደረጃ የሚያሻሽሉ የልማት ተግባራት ከወዲሁ ታስበው ሊከናወኑ እንደሚገባ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ 

በዚህም የከተማዋን መዋቅራዊ ፕላን በማሻሻል በውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችን በማሳተፍ በሪል ስቴት፣ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባ መክረዋል፡፡ 

የማእከላዊ ጎንደር ዞን የአካባቢውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን  በበጋ  መስኖ ስንዴ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በስራ እድል ፈጠራና የኑሮ ውድነትን በማረጋጋት ረገድ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን በጉብኝታቸው ወቅት መመልከታቸውን ተናግረዋል። 

ቡድኑ ባካሄደው የመስክ ግምገማ ላይ በመመስረትም ጠንካራ ጎኖች  እንዲቀጥሉና ድክመቶች እንዲታረሙ በቀጣይ ድጋፍ እንደሚደረግም ዶክተር ጌዲዮን አመልክተዋል፡ 

የማእከላዊ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወርቁ ሃይለማርያም በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ይዞት የመጣውን ጸጋ አስፍቶ ለመጠቀም ከጎንደር ዩንቨርሲቲ ጋር በመተባበር የጎርጎራ ከተማ የማስተር ፕላን ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡ 

ቡድኑ በዞኑ ተገኝቶ የልማትና የሰላም እንቅስቃሴውን መመልከቱም በቀጣይ የውጭና የአገር ውስጥ ባለሃብቶችን ለመሳብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝም ዋና አስተዳዳሪው አብራርተዋል። 

የቡድኑ አባልና የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በበኩላቸው ፕሮጀክቱ  የአካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማስተሳሰር ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ድርሻው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

በጎንደር ከተማ ለአንድ ቀን በተካሄደው የግምገማ መድረክ ላይ የዞኑ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውም ተመልክቷል፡፡ 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም