አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ እያስቻለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የደን ሽፋንን ለማሳደግ እያስቻለ ነው
ደሴ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦-የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን በማልማት የደን ሽፋንን ለማሳደግ ያስቻለ ውጤት መመዝገቡን የኢትዮጵያ ደን ልማት አስታወቀ፡፡
ወሎ ዩኒቨርሲቲ ዘጠነኛውን የደን ቀን "ደንና ፈጠራ" በሚል መሪ ሀሳብ እንግዶችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ዛሬ በደሴ ከተማ አክብሯል፡፡
በኢትዮጵያ ደን ልማት የደን ውጤቶች አጠቃቀምና ስርዓት ተከባሪነት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ቢተው ሽባባው በሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ የደን ልማት ለፍጥረታት ሁሉ መጠለያና ምግብ ማመቻቸት ነው።
በተጨማሪም ከለማው ደን መድሃኒት፣ ውሃ፣ መስኖና ለፋብሪካ ጥሬ እቃ ግብዓቶች ማግኛ ሃብት መሆኑን ጠቁመው፤ በእርሻ፣ ልቅ ግጦሽ፣ ከሰልና ቤት መስሪያ የሚመነጠረውን ደን ማስቀረት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተጀመረ ወዲህ የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን በመሸፈን አርሶ አደሩ የደን ልማቱን ተጠቅሞ በእንስሳት ማርባት፣ በንብ ማነብ ፣በመስኖና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ስራዎች በመሰማራት ተጠቃሚ እየሆነ ነው፡፡
"በየዓመቱ እስከ 92ሺህ ሄክታር መሬት የደን መመንጠር ያጋጥም የነበረውን አሁን ላይ ወደ 38ሺህ ሄክታር ዝቅ ማድረግ ተችሏል" ያሉት ስራ አስፈጻሚው፤ በኢትዮጵያ 54 ሚሊዮን ሄክታር የተራቆተ መሬት መኖሩን ጥናቶች እንደሚያሳዩ አመልክተዋል፡፡
የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን ለመሸፈን በሚደረገው ጥረትም የወሎ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ የደን ልማት ባለሙያ አቶ ካሴ ቢለን በበኩላቸው፤ ዞኑ ተራራዎች የሚበዙበት በመሆኑ የአፈር መከላትን ለመከላከል በየዓመቱ በተለዩ ተፋሰሶች ላይ ችግኝ የመትከልና የመንከባከብ ስራ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ከወሎ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመቀናጀት በተፋሰሶች ላይ የሚካሄደው የደን ልማት በጥናትና ምርምር በስልጠናና የግንዛቤ ፈጠራ ስራ አስፈላጊውን እገዛ እየተደረገ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የደን ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶክተር ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ከመንግስትና ሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የደን መጨፍጨፍና ውድመትን ለመከላከል እየሰራ ይገኛል፡፡
የተራቆቱ አካባቢዎችን በደን እንዲሸፈኑ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጡን በመቋቋም ለዜጎች ምቹ አካባቢ ለመፍጠር በቴክኖሎጂና በጥናት ጭምር የታገዘን ስራ በዩኒቨርሲቲው መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡
በዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ የሰለጠኑ ሙያተኞችን ከማፍራት በተጨማሪ ለዘርፉ አመራር አባላት ባለሙያዎችና ለሚመለከታቸው አካላት በደን ልማት አጠቃቀምና አያያዝ ላይ ያተኮረ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ አውስተዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የወሎ ዩኒቨርሲቲ የደቡብ ወሎ ዞን አመራር አባላትና የዘርፉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ተገኝተዋል።
አሁን ላይ የሀገሪቷ 17 ነጥብ 2 በመቶ የደረሰውን የደን ሽፋን በ2030 ዓ.ም ወደ 30 በመቶ ከፍ ለማድረግ ግብ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ህዝቡን በማሳተፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩን ማሳካት እንደሚገባ ገልጸዋል።