በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአምስት ዓመታት የሚተገበር "ስካይ-በርድ ሁለት" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ለአምስት ዓመታት የሚተገበር "ስካይ-በርድ ሁለት" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦በምስራቅ አፍሪካ ሶስት ሀገራት የሚተገበር "ስካይ-በርድ ሁለት" የተሰኘ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ፡፡
ፕሮጀክቱ በሴቶች እኩልነት እና አካታችነት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚተገበር ሲሆን በሶስት የአፍሪካ ሀገራት ላይ ተግባራዊ የሚደረገ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት አበራ ቶላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ "ስካይ-በርድ ሁለት" ፕሮጀክት ለአምስት ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል።
በሴቶች እኩልነትና አካታችነት ላይ ትኩረት በማድረግ በኢትዮጵያ፣ ሩዋንዳና ዩጋንዳ ተግባራዊ የሚደረገው ፕሮግራም ከ200 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ አራት ሚሊዮን ዩሮ የተመደበ ሲሆን 80 በመቶው በኦስትሪያ ልማት ማህበር እና ቀሪው 20 በመቶው ደግሞ በኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበርና በስዊዘርላንድ የተፈጥሮ ልማት የሚሸፈን ይሆናል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በቆይታው ሴቶች የአመራርና የውሳኔ ሰጪነት ሚና እንዲኖራቸው የሚያስችሉ የተቋማት ግንባታ ስራዎች በስፋት የሚሰራ ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በአንድ ቋት የመጠጥ ውሃ፣ ሳኒቴሽን እና ሃይጂን /WASH/ ፕሮጀክትን ይበልጥ ለማጠናከር፣ የሴቶችን አቅም ለማጎልበት ተሳትፎ ለማሳደግ እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
በኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ተመስገን አበበ በበኩላቸው፤ ተግባራዊ የተደረገው "ስካይ-በርድ 1" ከ210 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
የኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር "ስካይ-በርድ ሁለት" ፕሮጀክት ግቡን እንዲመታ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በሁሉም መስኮች ትብብር ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን የጠቆሙት ደግሞ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ዶክተር ሲሞን ክናፕ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በአዲስ አበባ ይፋ የተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ፕሬዝዳንት አበራ ቶላ፣ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕ (ዶ/ር)፣ በኦስትሪያ ቀይ መስቀል ማህበር የኢትዮጵያ ካንትሪ ዳይሬክተር ተመስገን አበበ እና የዩጋንዳና የሩዋንዳ ቀይ መስቀል ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡