በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን እና አስተናጋጅ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን እና አስተናጋጅ ማኅበረሰቦችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞችን የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችንና የአስተናጋጅ ማኅበረሰብ ክፍሎችን በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።
የፕሮጀክቱ ትግበራ የኔዘርላንድ መንግሥት ከኢትዮጵያ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት እና ሌሎች የሰብአዊና የልማት ኤጀንሲዎች ጋር በመተባበር የሚከናወን ነው።
የፕሮጀክቱ የመጀመሪያ ምዕራፍ ትግበራ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2020 እስከ 2023 የተከናወነ ሲሆን ሁለተኛው ምዕራፍ ደግሞ በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።
በዚህም በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገራት ስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችና የአስተናጋጅ ማኅበረሰብ ክፍሎች የተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
በይፋዊ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሄንክ ጃን ባከር፤ በፕሮጀክቱ ስደተኞችና ተቀባይ የማኅበረሰብ ክፍሎች የትምህርት የሙያ ሥልጠና፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ሌሎችም ድጋፍና እገዛዎች የሚደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራትን ስደተኞች ተቀብላ ማስተናገዷን ያደነቁት አምባሳደሩ፤ ለዚህ ደግሞ ኔዘርላንድ እገዛ የምታደርግ መሆኑን ገልፀዋል።
በመጀመሪያው ምዕራፍ ትግበራ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰው፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የላቀ አፈጻጸም እንዲኖር ይሰራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጠይባ ሀሰን፤ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የተለያዩ አገራትን ስደተኞች ተቀብላ እያስተናገደች ትገኛለች ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥትም ስደተኞችን ያሳተፈ የምጣኔ ኃብትና ማኅበራዊ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ልማት በመተግበር ላይ ይገኛል።
በዚህ ረገድ ከተለያዩ አጋር ደርጅቶች ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በኔዘርላንድ መንግሥትና አጋር ደርጅቶች የተጀመረው ፕሮስፔክት ፕሮጀክት አንዱ ነው ብለዋል።