ቀጥታ፡

ሰላምን ለማፅናትና በመልካም ስብዕና የታነፀ ትውልድ ለማፍራት  የሃይማኖት አባቶች ሚና መጠናከር ይገባዋል

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ ሰላምን ለማጽናትና  በመልካም ስብዕና የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሃይማኖት አባቶች ሚና መጠናከር እንደሚገባው  የሃይማኖት አባቶች ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የመቻቻልና የአብሮ መኖር እሴቶች መገለጫ ስትሆን የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ግጭትን የሚፈቱበትና የሚይዙበት ባህል ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑ ይታወቃል።

ይሁንና በአገሪቱ ያሉ የሰላም እሴቶችን ባለመጠቀምና የሃይማኖት አስተምህሮ በሚፈለገው ልክ ባለመሆኑ፤ በኢትዮጵያ የሚገጥሙ ፈተናዎችን ለመሻገር አዳጋች እየሆነ መምጣቱ ይገለጻል።

የኢትዮጵያውያንን ባህልና ወግ እንዲሁም በሀገሪቱ የሚገኙ መልካም እሴቶችን የሚያከብር ትውልድን በማፍራት ረገድ የተለያዩ ባለድርሻ አካላቶች ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ይታወቃል።

በተለይም  መልካም ስብዕና የተላበሰ ትውልድ እንደ ሀገር ከመቅረፅ አኳያ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎም በግንባር ቀደምነት ከሚነሱት ውስጥ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና የሃይማኖት ተቋማት  ዋነኞቹ ናቸው።

ኢዜአ ይህን መነሻ በማድረግ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ  በመልካም ስነ-ምግባር ከማነፅ አንጻር የሃይማኖት አባቶች እና የተቋማት ሚና በሚመለከት  የሃይማኖት አባቶችን አነጋግሯል። 

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ-ክህነት የዕቅድና ልማት መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቢ ሰላም ሰለሞን ቶልቻ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በሀገሪቱ የሚገኙ የእምነት ተቋማቶች መልካም ስብዕናን የተላበሱ ትውልዶችን ከመቅረፅ አንጻር ብዙ ሥራዎች ቢሰሩም በቂ ነው ማለት ግን አያስደፍርም ብለዋል። 

በሀገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ወጣቶች እንዳሉ ሁሉ መልካም እሴቶች የሚጥሱ ትውልዶች የሉም ማለት አይቻልም ነው ያሉት።


 

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ልዩ አማካሪና የሃይማኖት መምህር ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ  ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ትውልዱን በጥሩ ሰብዕና ማነፅ ላይ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።

ትውልድን በመልካም ስነ-ምግባር  በማነፅ እና በመቅረጽ ላይ ትልቅ ድርሻ ካላቸው ተዋናዮች ውስጥ የሃይማኖት አባቶች ትልቅ ሚና አለን ሲሉ ተናግረዋል።

አገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሟትን ችግሮች እንድትሻገር የሃይማኖት ተቋማቶች ትውልድ የመገንባት ሚናችንን  ልናሳድግ ይገባል፤ ወጣቱም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ የምንገኝ የሃይማኖት ተቋማቶች ሀገሩን የሚወድ ለሌሎች ቀና የሆነ ሰው በሚፈለገው ደረጃ አለማፍራታችን ሀገራችንን ለፈተና እየዳረጋት ይገኛል ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጄ ጀምበሩ ናቸው።


 

በአሁኑ ሰዓት ሁላችንም ኢትዮጵያውያንን መልካም ስነ-ምግባር ያላቸውን ትውልዶች ለማፍራት ያሉብንን ክፍተቶች በመሙላት ትውልዱ ላይ ለውጥ ማምጣት ካልቻልን ሀገሪቱን ከችግር ማላቀቅ አዳጋች ነው ሲሉ ተናግረዋል።

መጋቢ ሰላም ሰለሞን ሀገሪቱን ከውድቀት በመታደግ ወደ ተሻለ እድገት ለማሻገር  ትውልዱን ሊያንጹ የሚችሉ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ አክለዋል።

በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን የሚገኙ ወጣቶች በጊዜያቸው ለሀገራቸው እድገት ምን ለውጥ አመጣሁ ብለው እራሳቸውን መጠየቅና መፈተሽ እንደሚኖርባቸውም የተናገሩት ደግሞ ኡስታዝ አቡበከር ናቸው፡

እንደ ሀገር ማፍራት የምንፈልገውን ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት የሃይማኖት ተቋማቶች ብሎም ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በየአካባቢያችን የሚገኙ ልጆች እና ወጣቶች ላይ በእኔነት ስሜት  መሥራት አለብን ብለዋል የሃይማኖት አባቶቹ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም