ኢትዮጵያ በቡና ወጪ ንግድ በዓመት እስከ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢ የማግኘት አቅም አላት - የዘርፉ ተመራማሪ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከቡና ሀብት በዓመት እስከ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ሀብት እንዳላት የቡና ብዝሃ ህይወት ዘርፍ ተመራማሪ ዶክተር ታደሰ ወልደማርያም ገለጹ።

በዓለማችን በሚገኙ 50 አገራት ቡና የሚመረቱ ሲሆን ከ120 ሚሊዮን በላይ የዓለም ሕዝብ ከዘርፉ ኢንዱስትሪ ከሚገኝ ገቢ ኑሯቸውን እንደሚደጉሙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ጉባኤ(አንክታድ) መረጃ ያመለክታል።

ከተጠቀሰው አሃዝ 25 ሚሊየኑ አነስተኛ የቡና እርሻ ያላቸው አርሶ አደሮችና የቡና ሰራተኞች ሲሆኑ፤ ከነዚህ ውስጥ 50 በመቶው በአፍሪካ ይገኛሉ።

ከቡና አምራች አገራት መካከል የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን ያላት ሀብት ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚ የቡና ብዝሃ ሕይወት ባንክ እየተባለች እንድትጠራ አድርጓታል።

ኢትዮጵያ እንደ ቡና መገኛነቷና እንዳላት ምቹ ስነ- ምህዳር ከዘርፉ በሚፈለገው መጠን ተጠቃሚ እየሆነች አይደለም ። 

የቡና ብዝሃ ህይወት ተመራማሪ ዶክተር ታደሰ ወልደማርያም ኢትዮጵያ ሰፊ የቡና ብዝሃ ሕይወት ሀብት ያላት አገር እንደሆነችና ይህ ፀጋም የበለጠ ጥራትና ምርታማነትን ለማሻሻል የሚያግዝ እንደሆነ ይገልጻሉ።

በተለይም በቡና አብቃይ አካባቢ በሚገኝ ደን ውስጥ በርካታ የቡና ዘረመል(ጀነቲክ) ሃብት መኖሩን ጠቅሰው፤ እነዚህ ሀብቶች የቡና ዝርያን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል፡፡

የምርታማነትና የጥራት ጉድለት ለማሻሻል እንዲሁም የበሽታና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም በደንና በማሳ ውስጥ የሚገኙ የቡና ሀብቶችን ከመጠበቅ ባሻገር የጀነቲክ ላብራቶሪን ማዘመን ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያላት የቡና የብዝሃ ህይወት ፀጋ በመጠበቅና ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ ከተቻለ  እስከ 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር በዓመት ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችል ፀጋ መኖሩን ነው ተመራማሪው የገለጹት።

ለቡና ብዝሃ ሃብት ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

መንግስት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ጋር በመተባበር ባከናወናቸው ስራዎች የያዩ፣ የከፋ፣  የሸካና የመዥንገር የቡና ብዝሃ ሕይወት የተከለሉ ጥብቅ ደኖች እንዲኖራቸው መደረጉን ገልጸዋል።

የቡና ጀነቲክ ሃብት ከአየር ንብረት ለውጥ፣ ከተፈጥሮና ሰው ሰራሽ  ችግሮች ለመጠበቅ የሚያስፈልጉ ጥብቅ ደኖች እንደሚያስፈልጉ አመልክተዋል።

ቡና አምራች አርሶ አደሮች በቴክኖሎጂ ታግዘው የቡናውን ተፈጥሮ ጣዕምና ጥራት ጠብቀው እንዲያመርቱና ተጠቃሚነታቸው እንዲያድግ የባለሙያዎች ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል።

በሂደት ቡና አብቃይ ያልሆኑ የደጋ አከባቢዎች ወደ አብቃይነት እየተቀየሩ እንደሚመጡና ለዚህም የሚያስፈልገውን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ገቢ የምታገኝበትን የቡና ብዝሃ ሕይወታዊ ሃብትና ስርዓተ ምህዳር የመጠበቅ፣ የማልማትና በዘላቂት ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግ በምርምር የታገዘ ስራ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

በ2016 በጀት አመት 350 ሺህ ቶን ቡና በመላክ 1 ነጥብ 75 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት መታቀዱን ከኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም