ቀጥታ፡

የአድዋ ድል መታሰቢያ የሀገር ቋሚ ቅርስ ነው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን የወል ታሪክ የሰነደና በጥበብ የተገነባ የሀገር ቋሚ ቅርስ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራርና ሠራተኞች ተናገሩ።

የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች በዛሬው እለት የአድዋ ድል መታሰቢያን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሠራተኞች፤ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ የገዘፈ ታሪክ የሚታወስበት ታሪካዊ መሆኑን ገልፀዋል።

በመሆኑም ይህንን ታላቅ የሀገር ታሪክ የሚመጥን ቋሚ ቅርስ መገንባቱ የሚደነቅ ነው ብለዋል።


 

የአድዋ ድል መታሰቢያ የኢትዮጵያውያንን የወል ታሪክ የሰነደ በጥበብ የተገነባ የሀገር ቋሚ ቅርስ መሆኑንም ተናግረዋል።

በተቋሙ የብቃትና ሰው ኃብት ሥራ አስፈጻሚ ስበር አንዱአለም፤ የአድዋ ድል መታሰቢያ በድንቅ ኪነ-ህንፃዊ ውበትና የአዕምሮ ፈጠራ የታነፀ ዘመን ተሻጋሪ ቅርስ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት፣ የነበራቸውን ጀግንነት እና አጠቃላይ በጦርነቱ ወቅት የነበሩ ሁነቶችን ገላጭ በሆነ መልኩ የተገነባ መሆኑን አይተናል ብለዋል።

በተቋሙ የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ሥራ አስፈጻሚ ኤልሳቤጥ ገብረሥላሴ፤ በአድዋ ድል የሴቶች የላቀ ጥበብና ለድሉ የነበራቸው ሚና እንዲታወስ በማድረግ መታሰቢያው የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን ገልፀዋል።


 

በተቋሙ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያው መስፍን ሽፈራው፤ የድል መታሰቢያው በአድዋ ጦርነት ከ128 ዓመት በፊት የተፈፀመን ታሪክ ልዩ የፈጠራ ክህሎት በመጠቀም ያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።

የአሁኑ ትውልድም የሀገርን ምጣኔ ኃብትና እድገት የሚደግፍ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከድህነት ለመውጣት መታሰቢያው መማሪያ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ በወቅቱ በነበረው መሳሪያ እና በፈረስ የታገዘ ውጊያ የጀግኖች አርበኞችን ተጋድሎ የሰነደ መሆኑን ተናግረዋል።

የአድዋ ድል መታሰቢያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ የተመረቀ ሲሆን፤ ለሕዝብ ዕይታ ክፍት ተደርጎ በመጎብኘት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም