በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ሁለት ራስ ቅል ያለው ልጅ ተወለደ

ሀዋሳ፤ መጋቢት 12/2016 (ኢዜአ)፦ በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የንግስት እሌኒ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አንዲት እናት ሁለት ራስ ቅል ያለው ልጅ በሰላም ተገላግላለች።

በሆስፒታሉ የህጻናት ህክምና ክፍል ሃላፊ ዶክተር ባሳዝን ጣሰው እንደገለጹት፤ በሆስፒታሉ አንዲት እናት ሁለት ራስ ቅል ያለውን ህጻን ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ገደማ ተገላግላለች።

የአምስት ልጆች እናት የሆነችው ወላዷ ከአንገቱ በታች በኩል የተያያዘ ሁለት ራስ ያለው ሆኖ የተወለደው ሕፃን ስድስተኛዋ ልጇ መሆኑን ነው የገለጹት።

እናትም እንዲህ ዓይነት ክስተት መኖሩን ሳታውቅ ቆይታ ለህክምና ከመጣች በኋላ ያወቀች ሲሆን፤ በሆስፒታሉ ሃኪሞች እርዳታ በመለስተኛ ቀዶ ሕክምና መገላገሏን ተናግረዋል።


 

በትክክለኛ የእርግዝና ወራት ቆይታ የተወለደው ባለ ሁለት ራስ ሕጻን አራት ነጥብ ሁለት ኪሎ ግራም እንደሚመዝን ገልጸዋል።

የተወለደው ህጻን ጤንነት አሁን ላይ ችግር ባይኖረውም ወደፊት አፈጣጠሩ እክል ሊፈጥርበት እንደሚችል አመላካች ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ነገር ግን ተጨማሪ ምርመራዎች በማስፈለጋቸው የሐኪሞች ቡድን ምርመራና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

እንዲህ ዓይነት ያልተለመደ ክስተት በሆስፒታሉ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቅሰው፤ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሚወለዱ "ከአንድ መቶ ሺህ ህፃናት መካከል አንድ መሰል ክስተት ሊገጥም ይችላል" ብለዋል።

በቀጣይ  "ሕጻኑ  በሚደረግለት ሕክምና ሊለያይ ይችል ይሆን?" በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዶክተር ባሳዝን፤ "ሁለቱ ራስ አብዛኛውን የሰውነት ክፍል የተጋራ  በመሆኑ ሕክምናውን አስቸጋሪ ያደርገዋል" ብለዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም