ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማእከልነት ይበልጥ እያደገና እየተጠናከረ መጥቷል- የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር 

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦  የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማእከልነት ይበልጥ እያደገና እየተጠናከረ መምጣቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ፤ በዲፕሎማሲው መስክ የተደረጉ አበይት እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫውም የአዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማእከልነት ይበልጥ እያደገና እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በዚህም ሰሞኑን ኤምባሲያቸውን የከፈቱትን ኬፕ ቨርዴ እና አርሜኒያን ጨምሮ በአዲስ አበባ ኤምባሲያቸውን የከፈቱ ሀገራት ቁጥር 134 ደርሷል ብለዋል።

በሳምንቱ አዲስ የተሾሙ የ17 ሀገራት አዳዲስ አምባሳደሮች ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሹመት ደብዳቤያቸውን ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል።

የስዊዘርላድ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኢግናዚዮ ካሲስ፤ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ የኢትዮ - ስዊዘርላድ ሁለንተናዊ የትብብር ግንኙነት በሚጠናከርበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል። 


 

የሁለቱ ሀገራት የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እና ስዊዝርላንድ ታሪካዊ ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚያስችሉ ስራዎች የሚከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ 14 የስዊዝርላንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ መሆኑን ጠቁመው እኤአ በ2022 የሁለቱ ሀገራት የንግድ ልውውጥ ከ94 ሚሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

በተያዘው ሳምንት መጨረሻ የማልታ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኢያን ቦርግ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም