ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው 

ድሬዳዋ ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ስራዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸው ተገለጸ።

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች በሌማት ትሩፋት መርሃግብርና በሌሎች  ዘርፎች እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች የልማት ስራዎች በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን ለማሳካት የሚያስችሉ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሱልጣን ወሊ ተናገሩ።

በስራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመራ የፌደራል ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች የሱፐርቪዥን ቡድን በድሬዳዋ የልማት ስራዎችን እየተመለከተ ይገኛል።


 

በስራ ጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሱልጣን ወሊ እንደተናገሩት፤ የመስክ ጉብኝቱ በስድስት ወራት የተሰሩና በሪፖርት የቀረቡ የስራ አፈፃፀሞችን በተግባር ለማመሳከርና በቀጣይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በማረም የተሻለ ውጤት ለማምጣት ነው።


 

በድሬዳዋ ገጠር ቀበሌዎች የሌማት ትሩፋት መርሃግብር  አተገባበርና የሚስተዋለው ውጤት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ጥረቶች ለማሳካት የሚያግዝ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ በማህበር የተደራጁ ሴቶችና ወጣቶች በንብ ማነብ፣ በወተትና በእንቁላል ምርት፣ በከብት ማድለብና በዶሮ እርባታ ተሰማርተው እያስመዘገቡ ያሉት ውጤቶች ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ነው የገለፁት።

መርሃ ግብሩ  የተመጣጠነ የቤተሰብ ፍጆታን ከማሟላት በዘለል የገበያ ዋጋን በማረጋጋት ውስጥም ጉልህ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ከሌማት ትሩፋት መርሃ ግብሩ በተጨማሪ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የአነስተኛ መስኖና የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የገጠሩ ህብረተሰብ በአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ላይ ተሰማርተው የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ የተጀመሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ድሬዳዋ  ዝናብ አጠርና ሞቃታማ መሆኗን ተከትሎ ለተደጋጋሚ ድርቅና ጎርፍ አደጋ የተጋለጠች መሆኗን ጠቅሰው፤ ችግሩን ለመከላከልና የጎርፍ ውሃን ጥቅም ላይ ለማዋል በገጠር እየተሰሩ የሚገኙ ግድቦች አበረታችና ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው መሆናቸውን ነው የገለፁት።

ከዚህ ጎን ለጎን የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሳደግ አስተዳደሩ በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በመመደብ  ፕሮጀከቱን ወደ   ወሳኝ ምእራፍ ማድረሱን ጠቅሰዋል።

ነገር ግን የውሃ  መስመሮችን በመዝጋት የውሃ አቅርቦቱን እየተፈታተነ የሚገኘው ጨዋማ ንጥረ ነገር (ካልሺየም ባይካርቦኔት) ችግር በአስተዳደሩ አቅም ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ  የፌዴራል መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል።

የፌዴራል ባለስልጣናት የሱፐርቪዥን ቡድን አባላት ከስደት ተመልሰው በግብርና ስራ ላይ ተሰማርተው  እየሰሩ የሚገኙ አርሶ አደሮችንም አበረታትተዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው የገጠሩ ህብረተሰብ  የምግብ ዋስትናው በቤተሰብ ደረጃ እንዲረጋገጥ የተጀመሩ የተቀናጁ ልማቶች ለውጥ እያስገኙ ይገኛሉ ብለዋል።

ከፌዴራል መንግስትና ከልማት አጋሮች ጋር በመቀናጀት የተጀመሩ ስራዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በማከል።

በስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል የተመራው የሱፐርቪዥን ቡድን ዛሬም የመስክ ጉብኝቱን ቀጥሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም