ለዘንድሮ የሐጂ ጉዞ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ሁጃጆች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለዘንድሮ የሐጂ ጉዞ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ሁጃጆች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ ለዘንድሮ የሐጂ ጉዞ እስካሁን ከ10 ሺህ በላይ ሁጃጆች መመዝገባቸውን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።
የዘንድሮው 1 ሺህ 445ኛው የሐጂ ጉዞ ምዝገባ ከጥር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በመከናወን ላይ ሲሆን በጥቂት ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል።
የሐጅ ጉዞው የሚጀመረው ደግሞ ግንቦት 13 ቀን 2016 ዓ.ም መሆኑን ከጠቅላይ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሐጅና ኡምራ ዘርፍ ኃላፊ ሸህ አብዱልአዚዝ መሃመድ፤ ዘንድሮ የምዝገባና ሌሎችም አገልግሎቶች በተቀላጠፈ መልኩ እየተከናወኑ ነው ብለዋል።
ለሃጅና ኡምራ ተጓዦች ቀደም ሲል የነበሩትን 18 የምዝገባ ጣቢያዎች ወደ 27 በማሳደግ በየአቅራቢያው አገልግሎት የሚሰጥበት አሰራር ተፈጥሯልም ነው ያሉት።
በዚህም ለመመዝገብ ከታቀደው 12 ሺህ እስካሁን 10 ሺህ 100 ሁጃጆችን መመዝገብ መቻሉን ና በቀሪ ቀናት ሌሎችም አገልግሎት ፈላጊዎች መስተናገድ የሚችሉ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሁጃጆች የሐጅ ሥነ ስርአት ፈጽመው እስኪመለሱ ድረስ ያለውን አገልግሎት በተመለከተ መረጃ የሚሰጡ የዲጅታል አገልግሎቶች መጀመራቸውንም ተናግረዋል።
የምክር ቤቱ የስራ አስፈጻሚ አባል ዶክተር አንዋር ሙስጠፋ፤ በበኩላቸው በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ እስከ መመለሻው ድረስ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል።