በክልሉ የሚገኘውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚገኘውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት ዓመታት አበረታች ስራዎች ተከናውነዋል - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
ጋምቤላ ፤ መጋቢት 12/2016 (ኢዜአ)፦በጋምቤላ ክልል የሚገኘውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑት ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አስታወቁ።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድንና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ፍቃድ ከወሰዱት ከ700 በላይ ባለሃብቶች ውስጥ 285 የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውም ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ህዝቡን ከድህነት ለማውጣት፣ የውጭ ዕዳን ለመቀነስና የበለጸገች አገረ መንግሥት ገንብቶ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስረከብ እንዲቻል አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመተግበር ላይ ይገኛል።
ክልሎችም ይህንኑ የኢኮኖሚ ሪፎርም ተግብረው የህዝባቸውን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያላቸውን የሀብት አማራጭ በመለየትና ሕዝቦቻቸውን በማሳተፍ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴዎችን ለመረዳት ይቻላል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ የሚገኘውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት በማልማት ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ክልሉ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት ቢሆንም ከለውጡ በፊት የሀብቱ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን ጠቅሰው፤ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠራቸውን ምቹ አጋጣሚዎች በመጠቀም ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ሰፊ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ቀደም ሲል የብልሹ አሰራር ችግር የነበረበትን የኢንቨስትመንት ልማት በማጥራት አልሚ ባለሃብቶችን ወደ ክልሉ እንዲገቡና ልማቱ እንዲፋጠን በማድረግ ረገድ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከ702 በላይ ባለሃብቶች፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድንና ሌሎች የአገልግሎት ዘርፎች ፍቃድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ ከነዚህም ውስጥ 285 የሚሆኑት ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል።
ከለውጡ በፊት ተጀምረው ግንባታቸው የተጓተቱ የመስኖ ግድቦች፣ የቢሮ ህንፃዎችና ሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ በማድረግ በኩልም ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በክልሉ ያለውን ሰፊ የወርቅ ማዕድን ሀብት ልማት በማዘመን እንደ አገር በዘርፉ የታለመውን ግብ እውን ለማድረግም "ኢትኖማይኒንግ" የተሰኘ ዓለም አቀፍ ኩባንያን ጨምሮ ሌሎች ባለሃብቶች በልማቱ እንዲሰማሩ መደረጉን ገልጸዋል።