ቀጥታ፡

የኢፌዴሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ታላቁ ኒሻን ተበረከተላቸው

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንትና የጦር ሃይሎች ዋና አዛዥ ሳልቫ ኬር ማያርዲት የሀገሪቱን ታላቁን ኒሻን ለኢፌዴሪ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አበረከቱ።

በደቡብ ሱዳን ብሄራዊ ቤተ-መንግስት በተካሄደ ታላቅ ስነ-ስርዓት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ነፃነትና ሉአላዊነት መከበር ለከፈሉት ታላቅ የደም መስዋዕትነትና ድጋፍ ክብር ይገባቸዋል በማለት የሀገሪቱን ታላቅ ኒሻን ማበርከታቸው በስነ-ስርዓቱ ላይ ተገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኬር ይህንን ታላቅ ኒሻን በቤተ-መንግስታቸው ሲያበረክቱ እንደገለፁት ኢትዮጵያ በቸገረን ጊዜ ሁሉ መጠጊያችን መጠለያችን ናት ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።


 

ኢትዮጵያ ለዚህ ሀገራዊ ነፃነታችን ክብር የሆኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆቿን ህይወት ጭምር በመክፈል እንደሀገር እንድንቆም በማድረጋቸው ውለታቸውን መቼም ከፍለን የማንጨርሰው ነው ብለዋል።

ዛሬም ድረስ የሠራዊታችንን አቅም በመገንባት የውሰጥ ችግር ሲያጋጥመን ፈጥነው በመምጣት ችግራችንን የሚጋሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው ሲሉ ፕሬዚዳንቱ መናገራቸውም ተገልጿል።

ዛሬም ከጎናችን ያልተለዩና የቁርጥ ቀን ወንድሞቻችን ከመሆናቸውም በላይ በደም የተሳሰርን ማንም ሊፈታው የማይችል የአንድ ቤተሰብ ልጆች መሆናችንን የሚያረጋግጥ ሽልማታችን እንደሆነ መላው የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ህዝብ እንዲያውቅልን እንፈልጋለን ማለታቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።


 

በተጨማሪም ይህንን ታላቅ ሽልማት ለጀግናው የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የበላይ ሃላፊና የምስራቅ አፍሪካ ፊልድ ማርሻል ለሆኑት ለፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በደቡብ ሱዳን ህዝብ ስም ሳበረክት ታላቅ ኩራት ይሰማኛል በማለት መናገራቸውም ተጠቁሟል።

በስነ- ስርዓቱ ላይ የሀገሪቱ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም፣ የሀገሪቱ የደህንነት ከፍተኛ ሃላፊዎች፣ ጄኔራል መኮንኖችና የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ጄኔራል መኮንኖች መገኘታቸውም በመረጃው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም