የፀሐይ አውሮፕላን ሀገር ቤት መመለስ ለኢትዮጵያ ጉልህ የታሪክ አሻራና ለዘመኑ የአቬዬሽን ባለሙያዎች ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የፀሐይ አውሮፕላን ሀገር ቤት መመለስ ለኢትዮጵያ ጉልህ የታሪክ አሻራና ለዘመኑ የአቬዬሽን ባለሙያዎች ትልቅ የሞራል ስንቅ ነው
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ የፀሐይ አውሮፕላን ሀገር ቤት መመለስ ለኢትዮጵያ ጉልህ የታሪክ አሻራና ለዘመኑ የአቬዬሽን ባለሙያዎች ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑን የኢትዮጵያ አየር ኅይል አመራርና አባላት ተናገሩ።
በኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች ዕገዛ የተገነባችውና ፀሐይ ወይም ኢትዮጵያ አንድ የሚል ስያሜ የተሰጣት ፀሐይ አውሮፕላን ጠላት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ወደ ሮም መወሰዷ ይታወቃል።
አውሮፕላኗ ከ88 ዓመታት በኋላ በተደረገ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ በአድዋ ድል መታሰቢያ በክብር ተቀምጣ ትገኛለች።
የአድዋ ድል መታሰቢያን የጎበኙት የኢትዮጵያ አየር ኅይል አመራርና አባላት የፀሃይ ሀገር ቤት መግባት ለኢትዮጵያ ጉልህ የታሪክ አሻራና ለዘመኑ የአቬዬሽን ባለሙያዎች ደግሞ ትልቅ የሞራል ስንቅ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ አየር ኅይል የግሮቭ ስኳድሮን አዛዥና የበረራ መምህር ሻምበል ሠለሞን በየነ፤ ፀሐይ አውሮፕላን ስራ ላይ የተሰማሩት የኢትዮጵያ አየር ኅይል ቀደምት አባላት መሆናቸውን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሀገር የማዘመን ጥረት እንዲሁም የቴክኖሎጂና ፈጠራ ልህቀቱን የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘመኑ ፀሐይ መሰራቷ አባቶች የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለማስከበር በአቬዬሽን ዘርፍ የነበራቸውን ውጥን እንደሚያሳይ ነው የጠቆሙት።
የአየር ኅይል አባላቱም ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመመራት በተሻለ ቁመና እና ሞራል እንዲሰሩ የሚያነሳሳ ነው ብለዋል።
ሌሎች በጉብኝት ላይ የነበሩት የአየር ሃይል የቴክኒክ ባለሙያዎች ቢልጥማ በሬ፣ ሻምበል እህትነሽ ማርሸት እና ምክትል መቶ አለቃ ኤፍሬም ማሬ፤ ፀሐይ አውሮፕላን የአቬሽን ዘርፍ መነሻ ብቻ ሳትሆን የቀደምት የአየር ኅይል አባላትን የማድረግ አቅም የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከስምንት አስርት ዓመታት በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመልሳ በክብር መቀመጧ ከታሪክ እውቀት ባለፈ የዘርፉ መማሪያ ይሆናል ነው ያሉት።