ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ከሌሴቶ ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ታደርጋለች

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሌሴቶ ጋር የመጀመሪያ የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ዛሬ ያደርጋል።

የሁለቱ አገራት ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ከሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን ጋር  ለሚደረጉት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ ማድረጋቸው ይታወቃል።

ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾችም ከመጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሜዳ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጨረሻ ልምምዱን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ማድረጉንና 26ቱም ተጫዋቾችም በተሟላ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በግብጹ ዜድ ክለብ የሚጫወተው አቤል ያለው ቡድኑን በመቀላቀል የሁለት ቀናት ልምምድ አድርጓል።

ተጋጣሚው የሌሴቶ ብሔራዊ ቡድን በ59 ዓመቱ የአገሪቱ የቀድሞ አማካይ ተጫዋች ሌስሊ ኖቲሲ እየተመራ ይገኛል። 

ብሔራዊ ቡድኑ 23 ተጫዋቾችን ያካተተ ልዑካን ቡድን በመያዝ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን ትናንት በአዲስ አበባ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል።

ኢትዮጵያና ሌሴቶ የሚያደርጓቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር(ፊፋ) ኢንተርናሽናል ጨዋታነት የተመዘገቡ ሲሆን በገለልተኛ ኢንተርናሽናል ዳኞች እንደሚመራ ፌዴሬሽኑ ገልጿል።

ኢትዮጵያ በፊፋ ወርሃዊ የአገራት የእግር ኳስ ደረጃ 145ኛ፤ ሌሴቶ 148ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያና ሌሴቶ እ.አ.አ በ2022 ባደረጓቸው ሁለት ዓለም አቀፍ የወዳጅነት ጨዋታዎች በሁለቱም በተመሳሳይ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

ዛሬ የሚደረገውን የሁለቱን አገራት ጨዋታ የጅቡቲው መሐመድ ጉዌዲ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም የእድሳት ስራ ሙሉ ለሙሉ ባለመጠናቀቁ ጨዋታው ከሚዲያ ባለሙያዎችና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች በቀር ለተመልካች ዝግ እንደሚሆን ተገልጿል።

ኢትዮጵያና ሌሴቶ ሁለተኛ የአቋም መለኪያ ጨዋታቸው መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም