ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ዋስትና መሆን አለበት - የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም ዋስትና መሆን አለበት - የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
አዲስ አበባ ፤መጋቢት 12/2016(ኢዜአ)፦ ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም ዋስትና መሆን አለበት ሲል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ኮሙኒኬሽን አስታወቀ።
ቢሮው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባወጣው መግለጫ ሰላምን ለማረጋገጥ ኋላ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በማስወገድ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ሂደት ወሳኝ በመሆናቸው እያንዳንዱ ሰው ለሁሉም፣ ከሁሉም፣ በሁሉም የምትሆን ሀገር የመገንባት ግዴታውን መወጣት አለበት።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተሰጠ መግለጫ
*************************
ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም ዋስትና መሆን አለበት
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለዓመታት ከውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ጋር እየታገለች በከፍተኛ መስዋዕትነት ስታሸንፍ ለዛሬ ደርሳለች። የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች የውጭ ተግዳሮቶችን ተቋቁመው የሀገሪቱን ነፃነት ለማስጠበቅ በአንድነት ቆመው እንደተፋለሙ ታሪክ ይመሰክራል። ይህ ደግሞ ለዘመናት በጋራ ያዳበርነው እና ዛሬም አብሮን ያለ የጀግንነት ባህላችን ነው።
ይሁን እንጂ ውጫዊ ፈተናዎችን በጋራ እንዳሸነፍናቸው ውስጣዊ ተግዳሮቶቻችንንም በውይይት እና ነጻ ሀሳብ በማንሸራሸር መፍታት እንዳንችል በየዘመናቱ ሀገራችንን የመሩ መንግሥታት ይህንን ዕድል ባለመፍጠራቸው ለዘመናት በድህነት እና ችግር ውስጥ እንድንኖር ተገደናል፡፡ አሁንም የተለያዩ አካላት ነጠላ ትርክት እየተከተሉ የትናንቱ ኋላ ቀርነት አብሮን እንዲቀጥል እየሠሩ ነው።
ከለውጡ ወዲህ የትላንቱን የፖለቲካ ኋላ ቀርነት ለማስወገድ፣ ሰላምን ለማረጋገጥ፣ የብልፅግና ጉዞውን የተሳካ ለማድረግ እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም አለመግባባቶች እና ግጭቶች በውይይት እና በምክክር እንዲፈቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ሙሉ ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ እጆቹን ለሰላም ዘርግቶ፣ በሮቹን ለሰላም ከፍቶ የሰላም የጥሪ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 1 ሺህ 521 የሸኔ ተዋጊዎች የመልሶ ማቋቋም ሥልጠና ተሰጥቷቸው ወደ መደበኛ ህይወት በመመለስ ሰላማዊ ህይወት እየመሩ ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓትም ከ2 ሺህ በላይ ታጣቂዎች የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ተመልሰዋል፡፡
ለኦሮሞ ሕዝብ የሚበጀው የተገኘውን ድል ተባብሮ በመጠበቅ ለተሻለ ነገ በሕብረት መሥራት እንጂ እርስ በርስ መፋለም እና መጠፋፋት አይደለም። የኦሮሞ ሕዝብ አሁን ያለበት ተጨባጭ የትግል ምዕራፍ ለትጥቅ ትግል የሚያነሳሳም አይደለም፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ሲታገልላቸው የነበሩት ዋና ዋና ጥያቄዎች የተመለሱ ሲሆን፣ የቀሩትም በሂደት እየተመለሱ ይገኛሉ። መጠላለፍ እና እርስ በርስ መጠፋፋት እንደ ሀገር ያገኘነውን ድል ለመጠበቅ እና የዴሞክራሲ እና የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ፈተና እየሆኑ ናቸው።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አሁንም መነጋገር እና ችግሮችን በውይይት መፍታት የመጀመሪያ ምርጫው ነው፤ ለዚህም ጠንክሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ በቀጣይነት ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ውይይት የሚደረግ ሲሆን፣ ሀገራዊ ምክክሩ የተሳካ እንዲሆን ክልሉ የሚጠበቅበትን አስተዋፅኦ ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
ሰላምን ለማረጋገጥ ኋላ ቀር የፖለቲካ አስተሳሰቦችን በማስወገድ ሁሉን አቀፍ እና አሳታፊ ሂደት ወሳኝ በመሆናቸው እያንዳንዱ ሰው ለሁሉም፣ ከሁሉም፣ በሁሉም የምትሆን ሀገር የመገንባት ግዴታውን መወጣት አለበት። ለዚህም የጦር መሣሪያ በመታጠቅ ራስን አሸብሮ ሌሎችን ከማሸበር ወጥቶ ችግሮችን በውይይት እና በድርድር የመፍታት የቀድሞ ባህላችን እንደ ዘላቂ መፍትሔ መውሰድ ይገባል። ይህንንም አውን ለማድረግ በጫካ ውስጥ ያሉ የታጠቁ ኃሃይሎች በሙሉ በነባሩ የኦሮሞ ሕዝብ የችግር መፍቻ ጥላ ስር በመሳባሰብ ወደ ሰላም እንዲመለሱ በድጋሚ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
የክልላችን ሕዝቦች እና ምሁራንም ሰላም እና ልማቷ የተረጋገጠ ክልል ለመፍጠር የጀመራችሁትን ጥረት አጠናክራችሁ በመቀጠል አርአያነት ያለው እንቅስቃሴያችሁን እንድታስቀጥሉ እናሳስባለን።
አባቶቻችን የውጭ ወራሪን በአንድነት በመፋለም ነፃነቷን የጠበቀች ሀገር እንዳወረሱን እኛም የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር በጠላቶቻችን የተወጠነውን ሀገርን የመበተን ህልም አክሽፈን ለሀገራችን ብልጽግና መሥራት ይጠበቅብናል።
ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም ዋስትና በመሆን በወንድማማችነት መንፈስ የሀገራችንን ኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም ለማሳካት በጋራ እንሥራ፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ
መጋቢት 2016 ዓ.ም
አዲስ አበባ