ማህበሩ ለተፈናቀሉ ወገኖች 120 ኩንታል የጤፍ ዱቄት ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ማህበሩ ለተፈናቀሉ ወገኖች 120 ኩንታል የጤፍ ዱቄት ድጋፍ አደረገ
ደብረብርሀን ፤ መጋቢት 11 /2016 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 120 ኩንታል የጤፍ ዱቄት ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩ ተፈናቃዮችን ያደረገው ድጋፍ አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደሚገመት ተገልጿል።
በማህበሩ የሰሜን ሸዋ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዳምጠው እምሻው በሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ማህበሩ ችግሩ ከተከሰተ ጀምሮ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረስ ሃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።
የተደረገው ድጋፍ በኮሚቴዎች አማካኝነት ለሴቶችና ህጻናት ቅድሚያ በመስጠት እንደሚከፋፈል አስረድተዋል።
ማህበሩ ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ከህዝቡ ጋር በመተባበርም ለተፈናቃዮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።
የድጋፉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ዓለሚቱ ተረፈ በሰጡት አስተያየት፤ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፤ ዛሬ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል ።
በደብረ ብርሃን ከተማ 23 ሺህ የሚጠጉ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ተጠቁሟል።