ቀጥታ፡

በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነት ያስከትላል - ከፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም የህግ ተጠያቂነት የሚያስከትል መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት አስታወቀ።

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለአግባብ የወሰዱትን ገንዘብ ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦች መረጃ ላይ ክትትል በማድረግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እንደሚሰራም አገልግሎቱ ገልጿል።

የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕብረትም በጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በባንኩ ላይ የተፈፀመውን ያልተገባ ድርጊት ማውገዙ ይታወሳል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በባንኩ ላይ መጋቢት 7 ቀን 2016 ዓ.ም ያጋጠመውን ችግር ተከትሎ ጤናማ ያልሆኑ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች መደረጋቸውን ተገንዝቦ አስፈላጊውን ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛል።

አገልግሎቱ መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ ሲሆን የራሳቸው ያልሆነን ገንዘብ ያንቀሳቀሱና ወጪ ያደረጉ ግለሰቦች ገንዘቡን ተመላሽ እንዲያደርጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎም በርካቶች እየመለሱ መሆኑን ጠቁሟል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ተግባር የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊና የራስ አስመስሎ የማቅረብና የመጠቀም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ኃላፊነት ከተሰጣቸው ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 መሰረትም በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ/ንብረት መውረስ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ወንጀሉ ክብደት እስከ 25 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ መደንገጉን በመግለጫው አስታውሷል።

ልዩ ልዩ ወንጀሎችን በመፈጸም የተገኘን ገንዘብ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና መጠቀም በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ አገልግሎቱ በራሱ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የሚያከናውናቸውን ስራዎች አጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል በመግለጫው ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ችግር ማጋጠም ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ክፍተት ጤናማ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ ያደረጉና  ገንዘቡን ተመላሽ ያላደረጉ ግለሰቦችን መረጃ በመከታተል ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራም ያረጋግጣል።

ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገረው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ያቦነሽ፤ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ተግባርም በፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል።

በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ፤ የተፈፀመው ድርጊት ሁሉንም የማይወክል የጥቂቶች ጥፋት መሆኑንም አስረድቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም