የተማሪዎች ሕብረት በጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈፀመውን ያልተገባ ድርጊት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የተማሪዎች ሕብረት በጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈፀመውን ያልተገባ ድርጊት አወገዘ
አዲስ አበባ ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕብረት በጥቂት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላይ የተፈፀመውን ያልተገባ ድርጊት አወገዘ።
ሕብረቱ የተፈጸመው ድርጊት ፍፁም ተቀባይነት የሌለው የጥቂት ተማሪዎች ጥፋት መሆኑንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውስጥ አሠራሩን ለማዘመን ባደረገው እንቅስቃሴ ዓርብ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊቱን በተፈጠረ ስህተት ተገቢ ያልሆነ የገንዘብ እንቅስቃሴ መደረጉ ይታወቃል።
በዚሁ ሌሊት ከ490 ሺህ በላይ ጤናማ ያልሆነና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ልውውጥ እንደነበርም በባንኩ ተገልጿል።
በዚህ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ልውውጥና እንቅስቃሴ የአንዳንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጥቂት ተማሪዎች የተሳተፉ መሆኑም ይታወቃል።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገረው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሕብረት ፕሬዝዳንት ሚካኤል ያቦነሽ፤ በዚህ ድርጊት ላይ የተሳተፉ ተማሪዎች ተግባር በፍፁም ተቀባይነት የሌለውና የሚወገዝ መሆኑን ገልጿል።
በመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን የጠቀሰው ፕሬዝዳንቱ፤ የተፈፀመው ድርጊት ሁሉንም የማይወክል የጥቂቶች ጥፋት መሆኑን ተናግሯል።
በመሆኑም የተማሪዎቹን ያልተገባ ድርጊት የተማሪዎች ሕብረት በፅኑ ያወግዘዋል ብሏል።
በነበረው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ በማያውቁት መንገድ ተሳታፊ የነበሩ ተማሪዎች እንደነበሩ አንስቶ፤ የወሰዱትን ገንዘብ መመለስ እንደቻሉም ጠቅሷል።
በዚሁ ተግባር ላይ ተሳትፈው የነበሩ ሌሎች ተማሪዎችም በወቅቱ የተመዘበረውን የሀገርና የሕዝብ ኃብት በመመለስ ላይ መሆናቸውን ጠቅሶ፤ ገንዘቡን በማስመለስ ረገድ ሕብረቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሀገር ሁለንተናዊ አቅምና የልማት መሠረት መሆናቸውን የተናገረው የሕብረቱ ፕሬዝዳንት፤ በዚሁ ልክ ኃላፊነት ወስደው መንቀሳቀስ አለባቸው ሲልም አሳስቧል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ወጣቶች የነገ ሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው አደራቸውን በታማኝነት እንዲወጡም መልዕክቱን አስተላልፏል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ አብዛኛው ተማሪዎች በባንኩ በተደረገላቸው ጥሪ የወሰዱትን ገንዘብ እየመለሱ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተመላሽ ላደረጉ ተማሪዎች ባንኩ ምንም ዓይነት ክስ እንደማይመሰርትም አረጋግጠዋል።