ካፍ የአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት ላይ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ስራዎች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀቁ

402

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በአዲስ አበባ ስታዲየም እድሳት መመዘኛ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ እንዲከናወኑ ያስቀመጣቸው ስራዎች ሙሉ በሙሉ መጠናቀቃቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የካፍ ወይም የፊፋ የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙን እድሳት ስራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ተገልጿል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ፋሲሊቲ ልማትና አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አስማረ ግዛው የስታዲየሙን እድሳት በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ባስቀመጠው መመዘኛ መሰረት የእድሳትና የጥገና ስራ መከናወን ከጀመረ ከሁለት ዓመት በላይ ማስቆጠሩን አስታውሰዋል።

በዚህም ካፍ የሰጠውን አቅጣጫ ተከትሎ በመጀመሪያ ዙር የስታዲየሙ የመጫወቻ ሜዳ፣ የተፈጥሮ ሳር ንጣፍ፣ የተመልካች መጸዳጃ ቤት፣ የተጫዋቾች የመልበሻ ክፍልና የዳኞች የፀረ-አበረታች ቅመሞች ሕክምና ማዕከል ግንባታ መካሄዱን አመልክተዋል።


 

በእድሳቱ ሁለተኛ ምዕራፍ የተመልካች መቀመጫ፣ የመገናኛ ብዙሃን የስራ ክፍል (Media room)፣ የመብራቶች (ፓውዛዎች) እና በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ ስክሪን የመትከል፣ የክብርና ልዩ ክብር እንግዶች ፋሲሊቲዎች እንዲሁም ዘመናዊ የስታዲየም ውሃ ማጠጫ ስርዓት የመዘርጋት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

የምዕራፍ ሁለት እድሳት ከ97 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቅሰው ቀሪ ውስን ስራዎች በቅርቡ ይጠናቀቃሉ ብለዋል።

ከእግር ኳስ ጋር ከተያያዙ የእድሳት ስራዎች በተጨማሪ ነባሩን የአትሌቲክስ መሮጫ መም የመቀየር ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።

የመሮጫ መሙን ለመተካት የአስፋልትና የጠረጋ ዝግጅት ስራዎች መጠናቀቃቸውንና አጠቃላይ የመሮጫ ትራክ እድሳት በቅርቡ ይጠናቀቃል ብለዋል።

በፓሪስ ለሚካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ዝግጅት በስታዲየሙ ይጀመራል ነው ያሉት።

በተያያዘም በምዕራፍ ሶስት የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች፣ የበይነ መረብ የቲኬት ሽያጭና በቴክኖሎጂ የታገዘ የደህንነት ስርዓት መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች በስታዲየሙና ዙሪያ ያሉ የውጫዊ ገጽታ ስራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

ስራዎቹን ለማከናወን የሚያስችል ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣ የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው የግንባታ ስራው ከሶስት እስከ አራት ወራት ባለው ጊዜ ለማጠናቀቅ መታሰቡን አመልክተዋል።

ካፍ በምዕራፍ አንድ እና ሁለት የስታዲየሙ እድሳት መሟላት አለባቸው ያላቸው ስራዎች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውን ጠቁመዋል።

ካፍ በሁለት ዙር ከሰጣቸው ምክረ ሀሳቦች ውጪ በምዕራፍ ሶስት ከስታዲየሙ ውጪ የሚሰሩ መሰረተ ልማቶች ካፍ ባስቀመጣቸው መመዘኛዎች መሰረት ይገነባሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ስታዲየም በመዲናዋ እምብርት ላይ የሚገኝ በመሆኑ መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በሶስተኛው ዙር ግንባታ የስታዲየሙን የውጭ ገጽታ የማስዋብ ስራ እንደሚከናወን ጠቅሰዋል።

ለስታዲየሙ የመጀመሪያ ምዕራፍ እድሳት 47 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለሁለተኛው ምዕራፍ 190 ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አመልክተዋል።

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ወይም የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) የተቆጣጣሪ ቡድን የስታዲየሙ እድሳት ስራ ለመገምገም በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን መጋቢት 12 እና 15 ቀን 2016 ዓ.ም ከሌሴቶ ጋር የሚያደርጋቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታዲየም ይደረጋሉ ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም