የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት አላቸው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ - ኢዜአ አማርኛ
የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት አላቸው - አምባሳደር ደሴ ዳልኬ
አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦ ተጨማሪ የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች እና በድሬዳዋ ነፃ ንግድ ቀጠና ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ገለፁ።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ ጋር ኢንቨስትመንት ተኮር የበይነ መረብ ውይይት አድርገዋል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው በውይይቱም የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴ፤ የኢንቨስትመንት ፍሰትና የሪፎርም ስራዎች እንዲሁም የደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ያላቸው እንቅስቃሴ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሴ ዳልኬ በበኩላቸው ኮርፖሬሽኑ ያከናወናቸው የሪፎርም ተግባራት ለደቡብ ኮሪያ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታን መፍጠራቸውን አስታውሰው በዚህም ተጨማሪ ባለሀብቶች ኢንቨስት የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።
በተደረገው ውይይት ተጨማሪ የደቡብ ኮሪያ ኢንቨስተሮችን ለመሳብ የሚዘጋጁ መድረኮች ላይ በጋራ ለመስራት፤ አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ማድረግ እንዲሁም ሌሎች ኢንቨስትመንት ተኮር ስራዎችን በጋራ ለመስራት ከስምምነት መደረሱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን መረጃ ያመለክታል።