ቀጥታ፡

አቶ አደም ፋራህ የቻይና ህዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዝዳንትን ተቀብለው አነጋገሩ

አዲስ አበባ፤ መጋቢት 11/2016(ኢዜአ)፦የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የቻይና ህዝቦች የወዳጅ ሀገራት አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ሚስተር ያንግ ዋንሚንግን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ለልኡካን ቡድኑ ደማቅ አቀባበል ያደረጉት አቶ አደም የሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ታሪካዊ ግንኙነት በመንግስት ለመንግስት ደረጃም ሆነ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብት ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀዋል።

በሁሉም መስኮች ኢትዮጵያና ቻይና የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸውና ዘመናትን የተሻገረው የሁለቱ ሀገራት መርህ ለበስ ግንኙነት ወደ ተሻለ ትብብርና የጋራ ተጠቃሚነት እንዲሻገር ብልፅግና ፓርቲ ፍላጎት እንዳለው አንስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት በጋራ ጉዳዮች ላይ በመተባበር በዘላቂነት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስመዝገብ እየጣሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።

በርካታ የቻይና ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ እንደሚገኙ ጠቅሰው በመሰረተ ልማት፣ በትምህርት፣ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ ከቻይና ለተደረጉ ድጋፎች አመስግነዋል፡፡


 

በቀጣይም በፓርቲ እና በመንግስት ደረጃ ያሉ ግንኙነቶችን ወደ ሕዝብ ለሕዝብ ለማሻገር ጅምር ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

ለዚህም የከተሞች እህትማማችነት ስምምነቶች፣ የዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ የባህል ልውውጥ፣ የተማሪዎች የተግባራዊ እውቀት ልውውጥ እና የወጣቶች ልማት አስፈላጊዎች መሆናቸውንና ጠንካራ ሥራ ሊሰራባቸው እንደሚገባ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ እንደሆነች ገልጸው በዚህም መነሻነት የብሪክስ ሀገራትን ጥምረት እስከ መቀላቀል ያደረሰ ውጤት እንዳገኘች አንስተዋል።

በቀጣይም ከወዳጅ ሀገራት ባለሃብቶች ጋር መልማት የሚችሉና ዘርፈ ብዙ ውጤት የሚያስገኙ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዳሉም ጠቅሰዋል።


 

ያንግ ዋንሚንግ በበኩላቸው ብልጽግና ፓርቲ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ በከተማ ልማት እና በማህበራዊ መስኮች ያገኛቸው ድሎች በርካታ መሆናቸውን አንስተው ለተመዘገበው ስኬት ያላቸውን አክብሮት ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ብቻም ሳይሆን ለቀጠናው እና ለመላው አፍሪካ ትልቅ መነሻ ነጥብ መሆኗን በማንሳት በተለያዩ መስኮች ያሉ ግንኙነቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብሪክስ ሀገራት ጥምረት አባል መሆኗም ተጨማሪ የትብብር መስኮችን የሚፈጥር እንደሆነም ገልጸዋል።

በሕዝብ ለሕዝብ ደረጃ ግንኙነቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ቻይና ፍላጎት እንዳላት እና ለዚህም ማስፈፀሚያ ይሆን ዘንድ ከ9 የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ያለው የከተሞች ለከተሞች ግንኙነት ይበልጥ እንዲጎለብትና ከአዳዲስ ከተሞች ጋርም ግንኙነት ለመመስረት ብርቱ ፍላጎቶች እንዳሉ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ለቻይና ስትራቴጂክ አጋር እንደሆነችና በቀጣይም በሁሉም መስኮች ትብብርን በማጠናከር የሁለቱ ሀገራት የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቻይና መንግስት በኩል በትኩረት እንደሚሰራም ቃል መግባታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም