ፓርቲው የክልሉን ፀጋዎችና የመልማት ዕድሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ ነው

ዲላ፣መጋቢት 11/2016 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉት ፀጋዎችና የመልማት ዕድሎችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ እየሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ገለጸ።

በክልሉ በተለያዩ ዞኖች "ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና" በሚል መሪ ሃሳብ ፓርቲው የአባላት ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።

በፓርቲው የክልሉ ከፍተኛ አመራር ወይዘሮ ሰናይት ሰለሞን በዛሬው ዕለት በዲላ ከተማ በተጀመረው ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸው እንደገለፁት፤ ኮንፈረንሱ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከመንፈቅ በፓርቲው መሪነት በየዘርፉ የተመዘገቡ ድሎችን በቀሪ የምርጫ ዘመን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዓላማን ያደረገ ነው ።


 

በክልሉ በተጠቀሱት ዓመታት የብልፅግና ፓርቲ ጉዞ በድል የታጀበና ውጤት የተመዘገበበት ነው ብለዋል።

ፓርቲው ከተመረጠ ጊዜ አንስቶ ለህብረተሰቡ የገባውን ቃል ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በተለይ ክልሉ ያሉትን ፀጋዎችና የመልማት ዕድሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ አበረታች ውጤት የታየበት የልማት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነትን በማፅናት ችግሮችን በድልና በውጤት ተሻግሮ አዲሱን ክልል አፅንቶ ለማስቀጠል የተሄደበት ርቀትም ተሞክሮ የሚቀመርበትና ትምህርት የሚወሰድበት መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በሰላም፣ በምግብ ዋስትና፣ በአረንጓዴ አሻራ ልማት እንዲሁም በፍትሐዊ የልማት ተደራሽነት ዙሪያ ተጠቃሽ ለውጦች መመዝገባቸውን አስረድተዋል።

ይሁንና የኑሮ ውድነት፣ የወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራና ውስን ዘርፎች ዛሬም የክልሉ ፈተናዎች መሆናቸውን ያነሱት ወይዘሮ ሰናይት በቀጣይ የፓርቲው አባላትና አመራሩ ችግሮችን በማስወገድ ለተሻለ ውጤት መትጋት እንዳለበት አሳስበዋል።

ፓርቲው ከምስረታው ጊዜ አንስቶ ዘርፈ ብዙ የልማት ተግባራትን በማከናወን ለማህበረሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እየተጋ እንደሚገኝ ያነሱት ደግሞ ሌላው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር ዶክተር ዝናቡ ወልዴ ናቸው።


 

በተለይ ለህብረተሰቡ የአደረጃጃት ጥያቄ ተገቢና ፈጣን ምላሽ በመስጠት ህብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነትና እህትማማችነትን ማስቀጠል መቻሉን አብራርተዋል።

በፓርቲው መሪነት በጌዴኦ ዞንም በተለይ በግብርና ልማትና በሰላምና ፀጥታ ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዞኑ ከ780 በላይ አርሶ አደሮች ልዩ ጣዕም ቡና አዘጋጀተው በቀጥታ መሸጥ የሚያስችላቸውን ፍቃድ ማግኝታቸውን ለአብነት አንስተው በቀጣይ ለበለጠ ውጤት በትብብር መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በዲላ ከተማ እየተካሄደ ባለው የፓርቲው ኮንፈረንስ ላይ ከክልል፣ ከዞን እና ከወረዳ የመጡ የብልጽግና ፓርቲ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም