ቀጥታ፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ይዘው በባህር በር ዙሪያ የተጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት ያግዛል

ጂንካ ፤መጋቢት 11/ 2016 (ኢዜአ)፦  የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ይዘው በማስረጃ የተደገፉ ሞጋች ሀሳቦችን በማፍለቅ በባህር በር ዙሪያ የጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት እንደሚያግዙ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው ከውጪ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ''የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መብት ከጂኦፖለቲካ እና ከዓለም አቀፍ ህግ አንፃር'' በሚል መሪ ሀሳብ ምክክር አካሂዷል።


 

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ኢትዮጵያ የባህር በር ማጣቷ የትውልዱ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል።

ይህም ሁኔታ ኢትዮጵያን ለኢኮኖሚና ለዲፕሎማሲ ተጽዕኖ እንደዳረጋት ገልጸው፤ የትውልዱን ጥያቄ ለመመለስ አሁን ላይ በመንግስት የተወሰደው ቁርጠኛ አቋም የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ የመንግስት አካሄድ ተፈጻሚ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲው ጉዳዩ በህዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

ዛሬ የተዘጋጀው መድረክም ከዚህ ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፤ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንም በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ወጥ የሆነ ግንዛቤ ይዘው በማስረጃ የተደገፉ ሞጋች ሀሳቦችን በማፍለቅ በባህር በር ዙሪያ የተጀመረውን የዲፕሎማሲ ጥረት ማገዝ አለባቸው ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህጎች ተገቢነት ያለው መሆኑን አንስተዋል።

የባህር በር ለማግኘት የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አበረታች መሆኑን ገልጸው፤ ይህው ጥረት ውጤት እንዲያስገኝም የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

በዩኒቨርስቲው የታሪክ ተመራማሪ አቶ ዳኜ ጀማነህ፣ የባህር በር ጥያቄ ኢትዮጵያ  በዓለም አቀፍ ህግም አንዲት አገር የባህር በር የመጠቀም መብት እንዳላት አንስተው፤ ኢትዮጵያም ይህንኑ መብቷን ተጠቅማ የጀመረችውን ጥረት ማጠናከር እንዳለባት አብራርተዋል።

ምሁራንም የመፍትሄ ሐሳቦችን በማፍለቅ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ማገዝ እንዳለባቸው ገልፀው፤ ህዝቡም ጥረቱን መደገፍ እንዳለበት አንስተዋል።

ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ዳዊት ዮናስ፣ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በዓለም አቀፍ ህጎች ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ የተጀመረው ጥረትም ተገቢ ነው ብለዋል።

በውጪ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪ ዶክተር ሄኖክ ጌታቸው፣ በጂንካ ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው ውይይት የተነሱ ሀሳቦች በባህር በር ዙሪያ የሚወጡ ስትራቴጂዎች እና ፖሊሲዎች ግብአት የሚሆኑ ናቸው።

በባህር በር ዙሪያ የተጀመረውን ስኬታማ የዲፕሎማሲ ጉዞ ከዳር ለማድረስ ሁሉም ዜጋ ከመንግሥት ጎን በመቆም ለአፈጻጸሙ መትጋት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ምሁራን፣ ጥናት አቅራቢዎች፣ የአሪ ዞን እና የደቡብ ኦሞ ዞን ማህበረሰብ ተወካዮች እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ታድመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም